ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 42:7-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ከዐሥር ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።

8. ስለዚህ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንንና፣ ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጦር መኰንኖች ሁሉ እንዲሁም ሕዝቡን ሁሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ጠርቶ፤

9. እንዲህ አላቸው፤ “ልመናችሁን በፊቱ እንዳቀርብ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

10. ‘ባመጣሁባችሁ ጥፋት አዝኛለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፤ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም።

11. አሁን የሚያስፈራችሁን የባቢሎንን ንጉሥ አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ ይላል እግዚአብሔር፤

12. እርሱ እንዲምራችሁና ወደ አገራችሁ እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ።’

13. “እናንተ ግን፤ ‘በዚህች ምድር አንቀመጥም’ ብትሉና አምላካችሁን እግዚአብሔርን ባትታዘዙ፣

14. ደግሞም፣ ‘ጦርነት ወደማናይበት፣ የመለከት ድምፅ ወደማንሰማበትና ወደማንራብበት ወደ ግብፅ ምድር ሄደን በዚያ እንኖራለንጰ ብትሉ፣

15. እንግዲህ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ ግብፅ ለመሄድ ወስናችሁ እዚያ ለመቀመጥ ብትሄዱ፣

16. የፈራችሁት ሰይፍ በዚያ ያገኛችኋል፤ የሠጋችሁበት ራብ እስከ ግብፅ ድረስ ተከትሎአችሁ ይመጣል፤ በዚያም ትሞታላችሁ።

17. በዚያም ለመኖር ወደ ግብፅ ለመሄድ የወሰኑ ሁሉ በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር በእርግጥ ይሞታሉ፤ ከማመጣባቸውም ጥፋት አንድ እንኳ የሚተርፍ ወይም የሚያመልጥ አይገኝም።’

18. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ቍጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እንደ ፈሰሰ፣ እንዲሁ ወደ ግብፅ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ በእናንተ ላይ ይፈሳል፤ እናንተም የመነቀፊያና የድንጋጤ፣ የመረገሚያና የመዘባበቻ ምልክት ትሆናላችሁ፤ ይህንም ስፍራ ዳግመኛ አታዩም።’

19. “እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፤ እግዚብሔር፤ ‘ወደ ግብፅ አትሂዱ’ ብሎአችኋል፤ እኔም ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ ዕወቁ፤

20. ‘ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን፤ እርሱ ያለህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንታዘዛለን’ ብላችሁ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር በላካችሁኝ ጊዜ ሕይወታችሁን የሚያጠፋ ስሕተት ፈጸማችሁ።

21. እነሆ፤ ዛሬ በግልጥ ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን እግዚአብሔር አምላካችሁ ልኮኝ የነገርኋችሁን ሁሉ አሁንም አልታዘዛችሁም፤

22. እንግዲህ ሄዳችሁ ልትኖሩበት በፈለጋችሁት ስፍራ በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር እንደምትሞቱ በርግጥ ዕወቁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 42