ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 51:42-59 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

42. ባሕር በባቢሎን ላይ ይወጣል፤ሞገዱም እየተመመ ይሸፍናታል።

43. ከተሞቿ ሰው የማይኖርባቸው፣ዝርም የማይልባቸው፣ደረቅና በረሓማ ቦታ፣ባድማ ምድርም ይሆናሉ።

44. ቤልን በባቢሎን ውስጥ እቀጣለሁ፤የዋጠውን አስተፋዋለሁ፤ሕዝቦች ከእንግዲህ ወደ እርሱ አይጐርፉም፤የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል።

45. “ሕዝቤ ሆይ፤ ከመካከሏ ውጡሕይወታችሁን አትርፉ!ከአስፈሪው የእግዚአብሔር ቍጣ አምልጡ።

46. ወሬ በምድሪቱ ሲሰማ፣ተስፋ አትቍረጡ፤ አትፍሩም፤ገዥ በገዥ ላይ ስለ መነሣቱ፣ዐመፅም በምድሪቱ ስለ መኖሩ፣አንድ ወሬ ዘንድሮ፣ ሌላውም ለከርሞ ይመጣል፤

47. የባቢሎንን ጣዖታት የምቀጣበት ጊዜ፣በርግጥ ይመጣልና።ምድሯ በሙሉ ትዋረዳለች፤የታረዱትም በሙሉ በውስጧ ይወድቃሉ።

48. ሰማይና ምድር በውስጣቸውም ያለው ሁሉ፣በባቢሎን ላይ እልል ይላሉ፤አጥፊዎች ከሰሜን ወጥተው፣እርሷን ይወጓታልና፤”ይላል እግዚአብሔር።

49. “በምድር ሁሉ የታረዱት፣በባቢሎን ምክንያት እንደ ወደቁ፣ባቢሎንም በእስራኤል በታረዱት ምክንያት መውደቅ ይገባታል።

50. ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ፤ሂዱ! ጊዜ አትፍጁ፤በሩቅ ምድር ያላችሁ እግዚአብሔርን አስታውሱ፤ኢየሩሳሌምንም አስቧት።”

51. “ባዕዳን ሰዎች ወደ ተቀደሰው፣ወደ እግዚአብሔር ቤት ስለ ገቡ፣እኛ ተሰድበናል፤ዕፍረትም ፊታችንን ሸፍኖአል፤ውርደትም ተከናንበናል።”

52. “እንግዲህ ጣዖቶቿን የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፤”ይላል እግዚአብሔር፤“በምድሯም ሁሉ፤ቍስለኞች ያቃስታሉ።

53. ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣም፣ከፍ ያለ ምሽጓን ብታጠናክርም፣አጥፊዎች እሰድባታለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

54. “ከባቢሎን ጩኸት፣ከባቢሎናውያንምየ ምድር፣የታላቅ ጥፋት ድምፅ ይሰማል።

55. እግዚአብሔር ባቢሎንን ያጠፋታል፤ታላቅ ጩኸቷንም ጸጥ ያደርጋል።ሞገዳቸው እንደ ታላቅ ውሃ ይተማል፤ጩኸታቸውም ያስተጋባል።

56. በባቢሎን ላይ አጥፊ ይመጣል፤ጦረኞቿ ይማረካሉ፤ቀስታቸውም ይሰበራል፤ እግዚአብሔር ግፍን የሚበቀል፣ተገቢውንም ሁሉ የሚከፍል አምላክ ነውና።

57. ባለ ሥልጣኖቿንና ጥበበኞቿን፣ገዦቿንና መኳንንቷን፣ ጦረኞቿንም አሰክራለሁ፤ለዘላለም ይተኛሉ፤ አይነቁምም፤”ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ።

58. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ወፍራሙ የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል፤ከፍ ያሉት ደጆቿም በእሳት ይቃጠላሉ፤ሰዎቹ በከንቱ ይደክማሉ፤የሕዝቡም ልፋት ለእሳት ይሆናል።”

59. የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የንጉሡ የግቢ አስከልካይ የነበረው የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ ከንጉሡ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ የሰጠው መልእክት ይህ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 51