ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 7:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. መጻተኛውንና ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱንም ባትጨቍኑ፣ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም ባታፈሱ፣ የሚጐዷችሁን ሌሎች አማልክት ባትከተሉ፣

7. ለአባቶቻችሁ ለዘላለም ርስት አድርጌ በሰጠኋቸው ምድር፣ በዚህ ስፍራ አኖራችኋለሁ።

8. እናንተ ግን፣ ከንቱ በሆኑ የሐሰት ቃላት ታምናችኋል።”

9. “ ‘ትሰርቃላችሁ፤ ሰው ትገድላላችሁ፤ ታመነዝራላችሁ፤ በሐሰት ትምላላችሁ፤ ለበኣል ታጥናላችሁ፤ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ትከተላላችሁ፤

10. ስሜ ወደ ሚጠራበት ወደዚህ ቤት መጥታችሁ በፊቴ ትቆሙና “ደህና ነን”። እያላችሁ እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ታደርጋላችሁ።

11. ስሜ የሚጠራበት፣ ይህ ቤት በእናንተ ዘንድ የወንበዴዎች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፤ የምታደርጉትን ነገር አይቻለሁ ይላል እግዚአብሔር።

12. “ ‘እንግዲህ ቀድሞ የስሜ ማደሪያ አድርጌው ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ሴሎ ሂዱ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትንም እዩ።

13. እነዚህን ሁሉ ስታደርጉ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ደጋግሜ ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁኝም፤ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን አልመለሳችሁም።

14. ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ አሁንም ስሜ በተጠራበት ቦታ፣ በታመናችሁበት ቤተ መቅደስ፣ ለአባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁት በዚህ ስፍራ እንዲሁ አደርጋለሁ፤

15. ወንድሞቻችሁ የሆኑትን፣ የኤፍሬምን ሁሉ ሕዝብ እንዳስወገድሁ፣ እናንተንም ከፊቴ እጥላችኋለሁ።’

16. “እንግዲህ ስለማልሰማህ፣ ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን፤ አትማልድላቸውም።

17. እነርሱ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?

18. ለሰማይዋ ንግሥት ቂጣ ሊጋግሩ፣ ልጆች እንጨት ይለቅማሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶችም ሊጥ ያቦካሉ፤ ሊያስቈጡኝም ለሌሎች አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀርባሉ።

19. ለመሆኑ ይህን የሚያደርጉት እኔን ለማስቈጣት ነውን? ይላል እግዚአብሔር፤ “ይልቁን ይህን በማድረጋቸው በሚደርስባቸው ዕፍረት የሚጐዱት ራሳቸውን አይደለምን?

20. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ በሰውና በእንስሳ ላይ፣ በዱር ዛፍና በምድር ፍሬ ላይ ይፈሳል፤ ይነዳል፤ አይጠፋምም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 7