ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 6:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. በዚህም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ጣልቃ አትግቡ፤ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት የአይሁድ አገረ ገዥና የአይሁድ መሪዎች በቀድሞው ቦታ ላይ መልሰው ይሥሩት።

8. በተጨማሪም የአይሁድ መሪዎች ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና ሲሠሩ፣ እናንተ ምን እንደምታደርጉላቸው ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ ሥራውም እንዳይቋረጥ የእነዚህ ሰዎች ወጪ በሙሉ ከመንግሥት ግምጃ ቤትና ከኤፍራጥስ ማዶ ከሚገኘው ገቢ ላይ ይከፈል።

9. ለሰማይ አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆን ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ነገር፣ ማለት ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ተባዕት ጠቦቶችን ስጧቸው፤ እንዲሁም ስንዴው፣ ጨዉ፣ የወይን ጠጁና ዘይቱ በኢየሩሳሌም ያሉት ካህናት በሚጠይቋችሁ መሠረት ያለ ማቋረጥ በየቀኑ ይሰጣቸው።

10. ይህ የሚሆነው የሰማይ አምላክን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ ለንጉሡና ለወንድ ልጆቹም ደኅንነት እንዲጸልዩ ነው።

11. ደግሞም ይህን ትእዛዝ የሚለውጥ ማንም ሰው ቢኖር፣ ከቤቱ ምሰሶ ተነቅሎ በምሰሶው ላይ እንዲሰቀል፣ ስለ ወንጀሉም ቤቱ የቈሻሻ መጣያ እንዲሆን አዝዣለሁ።

12. ይህን ትእዛዝ ለማፍረስ ወይም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለማጥፋት እጁን የሚያነሣ ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ፣ ስሙን በዚያ እንዲኖር ያደረገ አምላክ ያጥፋው።እኔ ዳርዮስ በትጋት እንዲፈጸም ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

13. ከዚያም ንጉሡ ዳርዮስ ባዘዘው መሠረት በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሥራው በትጋት እንዲፈጸም አደረጉ።

14. ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተጽናኑ ሥራውን ቀጠሉ፤ የቤተ መቅደሱንም ሥራ በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ እንዲሁም የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፣ ዳርዮስና አርጤክስስ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ሠርተው ጨረሱ።

15. ይህም ቤተ መቅደስ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በሦስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።

16. ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና የቀሩትም ምርኮኞች የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ።

17. ለዚህ ለእግዚአብሔር ቤት ምረቃም አንድ መቶ ወይፈኖችን፣ ሁለት መቶ አውራ በጎችንና አራት መቶ ተባዕት ጠቦቶችን ሰጡ፤ ለመላው እስራኤል የኀጢአት መሥዋዕትም ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ልክ አቀረቡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 6