ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 9:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ መሪዎቹ ወደ እኔ መጥተው እንዲህ አሉኝ፤ “ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ የእስራኤል ሕዝብ ከጎረቤቶቻቸው ከከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኢያቡሳውያን፣ ከአሞናውያን ርኵሰት ራሳቸውን አልለዩም።

2. ሴቶቻቸውን ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ሚስት አድርገው ወስደዋል፤ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር ሕዝቦች ጋር ደባልቀዋል፤ በዚህ በደል ዋነኛ የሆኑትም መሪዎቹና ሹማምቱ ናቸው።”

3. እኔም ይህን በሰማሁ ጊዜ፣ መጐናጸፊያዬንና ካባዬን ቀደድሁ፤ የራሴን ጠጒርና ጢሜን ነጨሁ፤ እጅግ ደንግጬም ተቀመጥሁ።

4. በደል ከፈጸሙት ምርኮኞች የተነሣም በእስራኤል አምላክ ቃል የተንቀጠቀጡት ሁሉ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ እጅግ እንደ ደነገጥሁ በዚያው ተቀመጥሁ።

5. ከዚያም፣ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ የተቀደደውን መጐናጸፊያዬንና ካባዬን እንደ ለበስሁ በሐዘን ከተቀመጥሁበት ተነሣሁ፤ በጒልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጆቼን በመዘርጋት፣

6. እንዲህ ስል ጸለይሁ፤“አምላኬ ሆይ፤ ኀጢአታችን ከራሳችን በላይ ሆኖአል፤ በደላችንም እስከ ሰማያት ደርሶአል፤ አምላኬ ሆይ፤ ፊቴን ወደ አንተ ቀና ለማድረግ ፈራሁ፤ እጅግም ፈራሁ።

7. ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በደላችን ታላቅ ነው። ከኀጢአታችንም የተነሣ፣ ዛሬ እንደሆነው ሁሉ እኛም ሆንን፣ ነገሥታቶቻችንና ካህናቶቻችን በባዕዳን ነገሥታት እጅ ወድቀን ለሰይፍ፣ ለምርኮ፣ ለብዝበዛና ለውርደት ተዳርገናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 9