ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 10:5-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. እነርሱም መጥተው ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ ሟቾቹ የክህነት ቀሚሳቸውን እንደ ለበሱ ተሸክመው ከሰፈር ወደ ውጭ አወጧቸው።

6. ሙሴም አሮንንና የአሮንን ልጆች፣ አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቊጣ እንዳይመጣ ጠጒራችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ስላጠፋቸው ሰዎች ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ሊያለቅሱላቸው ይችላሉ።

7. የእግዚአብሔር (ያህዌ) የመቅቢያ ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን አትውጡ።” እነርሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ።

8. እግዚአብሔርም (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤

9. “እንዳትሞቱ አንተና ልጆችህ ወደ መገናኛው ድንኳን በምትገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም በልጅ ልጃችሁ ዘንድ የሚጠበቅ ዘላለማዊ ሥርዐት ነው።

10. የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን፣ ርኵሱንና ንጹሑን ለዩ፤

11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤላውያን አስተምሩ።

12. ሙሴም አሮንንና የተረፉትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው የእህል ቊርባን የቀረውን ወስዳችሁ ያለ እርሾ ጋግሩት፤ እጅግ ቅዱስ ስለ ሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 10