ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 10:24-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. የብንያም ነገድ ሰራዊት አለቃም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበር።

25. በመጨረሻም የዳን ሰፈር ሰራዊት ለሁሉም ክፍሎች የኋላ ደጀን በመሆን በዐርማቸው ሥር ተጓዙ፤ አለቃቸውም የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበር።

26. እንዲሁም የአሴር ነገድ ሰራዊት አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበር።

27. እንዲሁም የንፍታሌም ነገድ ሰራዊት አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበር።

28. እንግዲህ የእስራኤል ሰራዊት የጒዞ አሰላለፍ ሥርዐት ይህ ነበር።

29. በዚህ ጊዜ ሙሴ የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን፣ “እነሆ፤ እግዚአብሔር፣ (ያህዌ) ‘እሰጣችኋለሁ’ ወዳለን ምድር ጒዞ ጀምረናል፤ በመልካም ሁኔታ ስለምናኖርህ ከእኛ ጋር ሂድ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእስራኤል በጎ ነገር ለማድረግ ቃል ገብቶአልና አለው።”

30. እርሱም መልሶ፣ “ይህስ አይሆንም፤ አልሄድም፤ ወደ አገሬና ወደ ወገኖቼ ተመልሼ እሄዳለሁ” አለው።

31. ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ አትለየን፤ በምድር በዳ ውስጥ የት መስፈር እንደሚገባን አንተ ታውቃለህ፤ ዐይናችንም ትሆናለህ።

32. ከእኛ ጋር ብትሄድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛም እናደርግልሃለን።”

33. ስለዚህ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ተራራ ተነሥተው የሦስት ቀን መንገድ ተጓዙ፤ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል ኪዳን ታቦትም በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ የሚያርፉበትን ቦታ በመፈለግ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር።

34. ከሰፈራቸው በሚነሡበት ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ደመና ቀን ቀን ከላያቸው ነበር።

35. ታቦቱ ለጒዞ በተነሣ ጊዜ ሁሉ ሙሴ፣“እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ተነሥ!ጠላቶችህ ይበተኑ፤የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ” ይል ነበር።

36. ባረፉ ጊዜም፣“እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤በብዙ ሺህ ወደሚቈጠሩት እስራኤላውያን ተመለስ” ይል ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 10