ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 10:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. “መለከቶቹን ካህናቱ የአሮን ልጆች ይንፉ፤ ይህም ለእናንተና ለሚመጡት ትውልድ የዘላለም ሥርዐት ይሁን።

9. በገዛ ምድራችሁ በግፍ በመጣባችሁ ጠላት ላይ ስትዘምቱ መለከቶቹን ከፍ ባለ ድምፅ ንፉ፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) በአምላካችሁ (ኤሎሂም) ትታሰባላችሁ፤ ከጠላታችሁም እጅ ትድናላችሁ።

10. እንዲሁም በደስታችሁ ቀናት ማለት በተደነገጉት በዓሎቻችሁና የወር መባቻ በዓል ስታከብሩ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በኅብረት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቱን ንፉ፤ እነዚህም በአምላካችሁ (ኤሎሂም) ፊት መታሰቢያ ይሆኑላችኋል። እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላካችሁ (ኤሎሂም) ነኝ።”

11. በሁለተኛው ዓመት፣ ሁለተኛው ወር በገባ በሃያኛው ቀን ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ።

12. ከዚያም እስራኤላውያን ከሲና ምድረ በዳ ተነሥተው ደመናው በፋራን ምድረ በዳ እስኪያርፍ ድረስ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ተጓዙ።

13. እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረትም ለመጀመሪያ ጊዜ ተጓዙ።

14. በመጀመሪያ የይሁዳ ሰፈር ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ሆነው ተጓዙ፤ አለቃቸውም የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበር።

15. የይሳኮር ነገድ ሰራዊት አለቃም የሰገር ልጅ ናትናኤል ነበር።

16. እንዲሁም የዛብሎን ነገድ ሰራዊት አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበር።

17. ከዚህ በኋላ ማደሪያው ተነቀለ፤ ድንኳኑን የተሸከሙት ጌድሶናውያንና ሜራሪያውያንም ጒዞ ጀመሩ።

18. ቀጥሎም የሮቤል ሰፈር ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ሆነው ተጓዙ፤ አለቃቸውም የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበር።

19. የስምዖን ነገድ ሰራዊት አለቃም የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበር።

20. እንዲሁም የጋድ ነገድ ሰራዊት አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበር።

21. ከዚህ በኋላ ቀዓታውያን ንዋያተ ቅዱሳቱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነርሱ ከመድረሳቸው በፊት ማደሪያው ተተክሎ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 10