ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 10:9-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. በገዛ ምድራችሁ በግፍ በመጣባችሁ ጠላት ላይ ስትዘምቱ መለከቶቹን ከፍ ባለ ድምፅ ንፉ፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) በአምላካችሁ (ኤሎሂም) ትታሰባላችሁ፤ ከጠላታችሁም እጅ ትድናላችሁ።

10. እንዲሁም በደስታችሁ ቀናት ማለት በተደነገጉት በዓሎቻችሁና የወር መባቻ በዓል ስታከብሩ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በኅብረት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቱን ንፉ፤ እነዚህም በአምላካችሁ (ኤሎሂም) ፊት መታሰቢያ ይሆኑላችኋል። እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላካችሁ (ኤሎሂም) ነኝ።”

11. በሁለተኛው ዓመት፣ ሁለተኛው ወር በገባ በሃያኛው ቀን ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ።

12. ከዚያም እስራኤላውያን ከሲና ምድረ በዳ ተነሥተው ደመናው በፋራን ምድረ በዳ እስኪያርፍ ድረስ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ተጓዙ።

13. እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረትም ለመጀመሪያ ጊዜ ተጓዙ።

14. በመጀመሪያ የይሁዳ ሰፈር ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ሆነው ተጓዙ፤ አለቃቸውም የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበር።

15. የይሳኮር ነገድ ሰራዊት አለቃም የሰገር ልጅ ናትናኤል ነበር።

16. እንዲሁም የዛብሎን ነገድ ሰራዊት አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበር።

17. ከዚህ በኋላ ማደሪያው ተነቀለ፤ ድንኳኑን የተሸከሙት ጌድሶናውያንና ሜራሪያውያንም ጒዞ ጀመሩ።

18. ቀጥሎም የሮቤል ሰፈር ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ሆነው ተጓዙ፤ አለቃቸውም የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበር።

19. የስምዖን ነገድ ሰራዊት አለቃም የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበር።

20. እንዲሁም የጋድ ነገድ ሰራዊት አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበር።

21. ከዚህ በኋላ ቀዓታውያን ንዋያተ ቅዱሳቱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነርሱ ከመድረሳቸው በፊት ማደሪያው ተተክሎ ነበር።

22. ቀጥሎም የኤፍሬም ሰፈር ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ሆነው ተጓዙ፤ አለቃቸውም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበር።

23. እንዲሁም የምናሴ ነገድ ሰራዊት አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበር።

24. የብንያም ነገድ ሰራዊት አለቃም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበር።

25. በመጨረሻም የዳን ሰፈር ሰራዊት ለሁሉም ክፍሎች የኋላ ደጀን በመሆን በዐርማቸው ሥር ተጓዙ፤ አለቃቸውም የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበር።

26. እንዲሁም የአሴር ነገድ ሰራዊት አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበር።

27. እንዲሁም የንፍታሌም ነገድ ሰራዊት አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበር።

28. እንግዲህ የእስራኤል ሰራዊት የጒዞ አሰላለፍ ሥርዐት ይህ ነበር።

29. በዚህ ጊዜ ሙሴ የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን፣ “እነሆ፤ እግዚአብሔር፣ (ያህዌ) ‘እሰጣችኋለሁ’ ወዳለን ምድር ጒዞ ጀምረናል፤ በመልካም ሁኔታ ስለምናኖርህ ከእኛ ጋር ሂድ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእስራኤል በጎ ነገር ለማድረግ ቃል ገብቶአልና አለው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 10