ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 14:19-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ከግብፅ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው ሁሉ እንደ ፍቅርህ ታላቅነት መጠን እባክህ አሁንም የዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።”

20. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር ብያቸዋለሁ፤

21. ይሁን እንጂ ሕያው እንደ መሆኔና የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ምድርን ሁሉ የሞላ እንደ መሆኑ መጠን፣

22. ክብሬን ደግሞም በግብፅና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ታምራት አይተው ካልታዘዙኝና ዐሥር ጊዜ ከተፈታተኑኝ ሰዎች አንዳቸውም፣

23. ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም። የናቀኝ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ አያያትም፤

24. አገልጋዬ ካሌብ ግን የተለየ መንፈስ ስላለውና በፍጹም ልቡ የተከተለኝ በመሆኑ ሄዶባት ወደ ነበረችው ምድር አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ይወርሷታል።

25. አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው የሚኖሩ ስለ ሆነ በነገው ዕለት ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።”

26. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

27. “ይህ ክፉ ማኅበረሰብ በእኔ ላይ የሚያጒረመርመው እስከ መቼ ነው? የእነዚህን ነጭናጮች እስራኤላውያን ማጒረምረም ሰምቻለሁ።

28. ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ስትናገሩ የሰማኋችሁን እነዚያን ነገሮች አደርግባችኋለሁ፤

29. በተደረገው ቈጠራ መሠረት፣ ሃያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናችሁና በእኔም ላይ ያጒረመረማችሁ ሁሉ በድናችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል።

30. መኖሪያችሁ እንድትሆን በጽኑ ወደ ማልሁላችሁ ምድር ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር ከእናንተ አንዳችሁም አትገቡባትም።

31. ይማረካሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን ግን አገባቸዋለሁ፤ እናንተ የናቃችኋትን ምድር እነርሱ ይደሰቱባታል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 14