ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 16:15-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ሙሴም በጣም ተቈጣ፤ እግዚአብሔርንም (ያህዌ) “ቊርባናቸውን አትቀበል፤ እኔ ከእነዚህ ሰዎች የወሰድኩት አንድ አህያ እንኳ የለም፤ አንዳቸውንም አልበደልሁም” አለ።

16. ሙሴም ቆሬን እንዲህ አለው፤ “አንተና ተከታዮችህ እንዲሁም አሮን ነገ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ትቀርባላችሁ።

17. እያንዳንዱም ሰው ጥናውን ይወስዳል፤ ባጠቃላይ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች ይሆናሉ፤ በዚያም ላይ ዕጣን ጨምሮ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቀርባል፤ አንተና አሮንም ጥናዎቻችሁን እንደዚሁ ታቀርባላችሁ።

18. እያንዳንዱ ሰው ጥናውን በመያዝ ፍም አድርጎበት፣ ዕጣን ጨምሮበት ከሙሴና ከአሮን ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ።

19. ቆሬም እነርሱን በመቃወም ተከታዮቹን ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር ለመላው ማኅበር ተገለጠ።

20. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

21. “ሁሉንም በአንድ ጊዜ እንዳጠፋቸው እናንተ ከዚህ ማኅበር ተለዩ።”

22. ሙሴና አሮን ግን በግንባራቸው ተደፍተው፣ “የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መንፈስ አምላክ (ኤሎሂም) የሆንህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ አንድ ሰው ኀጢአት በሠራ በመላው ማኅበር ላይ ትቈጣለህን?” ሲሉ ጮኹ።

23. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

24. “ማኅበሩን ‘ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ራቁ’ በላቸው።”

25. ሙሴ ተነሥቶ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት።

26. እርሱም፣ “ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳን ራቍ የእነርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ፤ ያለበለዚያ በእነርሱ ኀጢአት ሁሉ እናንተም ትጠፋላችሁ” ሲል ማኅበሩን አስጠነቀቀ።

27. ስለዚህ እነርሱ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን ራቁ። ዳታንና አቤሮን ወጥተው ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃናቶቻቸው ጋር በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ነበር።

28. ሙሴም እንዲህ አለ፤ “እነዚህን ነገሮች ሁሉ እንዳደርግ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ላከኝና ከራሴም እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ፤

29. እነዚህ ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው አሟሟት የሚሞቱ ቢሆኑና በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሰው ብቻ የሚደርስባቸው ከሆነ፣ እኔን እግዚአብሔር (ያህዌ) አልላከኝም።

30. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ አዲስ የሆነ ነገር አምጥቶ ምድር አፏን ከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥና በሕይወታቸው ወደ መቃብር ቢወርዱ፣ ሰዎቹ እግዚአብሔርን (ያህዌ) የናቁ መሆናቸውን የምታውቁት ያን ጊዜ ነው።”

31. ይህን ሁሉ ተናግሮ እንደ ጨረሰ የቆሙባት ምድር ተሰነጠቀች፤

32. አፏንም ከፍታ ሰዎቹን ከነቤተ ሰቦቻቸው እንዲሁም የቆሬን ሰዎች በሙሉ፣ ንብረታቸውንም ሁሉ ዋጠች።

33. እነርሱም ካላቸው ከማናቸውም ነገር ጋር ከነሕይወታቸው ወደ መቃብር ወረዱ፤ ምድሪቱም በላያቸው ተከደነችባቸው፤ ጠፉ፤ ከማኅበረ ሰቡም ተወገዱ።

34. ከጩኸታቸውም የተነሣ በአካባቢያቸው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ምድሪቱ እኛንም እኮ ልትውጠን ነው” ብለው ሸሹ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 16