ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 16:25-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ሙሴ ተነሥቶ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት።

26. እርሱም፣ “ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳን ራቍ የእነርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ፤ ያለበለዚያ በእነርሱ ኀጢአት ሁሉ እናንተም ትጠፋላችሁ” ሲል ማኅበሩን አስጠነቀቀ።

27. ስለዚህ እነርሱ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን ራቁ። ዳታንና አቤሮን ወጥተው ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃናቶቻቸው ጋር በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ነበር።

28. ሙሴም እንዲህ አለ፤ “እነዚህን ነገሮች ሁሉ እንዳደርግ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ላከኝና ከራሴም እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ፤

29. እነዚህ ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው አሟሟት የሚሞቱ ቢሆኑና በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሰው ብቻ የሚደርስባቸው ከሆነ፣ እኔን እግዚአብሔር (ያህዌ) አልላከኝም።

30. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ አዲስ የሆነ ነገር አምጥቶ ምድር አፏን ከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥና በሕይወታቸው ወደ መቃብር ቢወርዱ፣ ሰዎቹ እግዚአብሔርን (ያህዌ) የናቁ መሆናቸውን የምታውቁት ያን ጊዜ ነው።”

31. ይህን ሁሉ ተናግሮ እንደ ጨረሰ የቆሙባት ምድር ተሰነጠቀች፤

32. አፏንም ከፍታ ሰዎቹን ከነቤተ ሰቦቻቸው እንዲሁም የቆሬን ሰዎች በሙሉ፣ ንብረታቸውንም ሁሉ ዋጠች።

33. እነርሱም ካላቸው ከማናቸውም ነገር ጋር ከነሕይወታቸው ወደ መቃብር ወረዱ፤ ምድሪቱም በላያቸው ተከደነችባቸው፤ ጠፉ፤ ከማኅበረ ሰቡም ተወገዱ።

34. ከጩኸታቸውም የተነሣ በአካባቢያቸው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ምድሪቱ እኛንም እኮ ልትውጠን ነው” ብለው ሸሹ።

35. እሳትም ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወርዳ የሚያጥኑትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላቻቸው።

36. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

37. “ጥናዎቹ የተቀደሱ ናቸውና ከተቃጠሉት ሰዎች ዘንድ ወስደህ በውስጣቸው ያለውን ፍም አርቆ እንዲደፋ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር ንገረው፤

38. እነዚህም ሕይወታቸውን ለማጥፋት ኀጢአት የሠሩ ሰዎች ጥና ናቸው፤ ጥናዎቹም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የቀረቡና የተቀደሱ በመሆናቸው ለመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጥቅጠህ አሣሣቸው፤ እነዚህም ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያ ይሁኑ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 16