ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 16:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እነዚህም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ግንባር ፈጥረው በመምጣት፣ “ምነው ከልክ አላለፋችሁም? የማኅበረ ሰቡ አባላት ሁሉ እያንዳንዳቸው የተቀደሱ ናቸው፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከእነርሱ ጋር ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ማኅበር ላይ የምትታበዩት ለምንድ ነው?” አሉአቸው።

4. ሙሴም ይህን ሲሰማ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤

5. ቆሬንና ተከታዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእርሱ የሆነውና የተቀደሰው ማን መሆኑን እግዚአብሔር (ያህዌ) ነገ ጠዋት ይለያል፤ ወደ ራሱም ያመጣዋል፤ የሚመርጠውን ሰው ወደ ራሱ እንዲቀርብ ያደርገዋል።

6. ቆሬ፣ አንተና ተከታዮችህ ሁሉ እንዲህ አድርጉ፤ ጥናዎችን ውሰዱ፤

7. በማግስቱም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እሳትና ዕጣን ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚመርጠውም ያ ሰው ቅዱስ ይሆናል፤ እናንት የሌዊ ልጆች፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ናችሁ።”

8. ደግሞም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፤ “እናንት ሌዋውያን አድምጡ

9. የእስራኤል አምላክ (ኤሎሂም) እናንተን ከቀሩት እስራኤላውያን ማኅበረሰብ መለየቱና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ማደሪያ አገልግሎት እንድትፈጽሙ ወደ ራሱ ማቅረቡ፣ እንድታገለግሏቸውም በማኅበረ ሰቡ ፊት እንድትቆሙ ማድረጉ አይበቃችሁምን?

10. አንተንና ከአንተም ጋር ወገኖችህ የሆኑትን ሌዋውያንን ሁሉ ወደ ራሱ አቅርቧችኋል፤ እናንተ ግን የክህነቱንም ሥራ ደርባችሁ ለመያዝ ይኸው ትሯሯጣላችሁ።

11. አንተና ተከታዮችህ ሁሉ አባሪ ተባባሪ ሆናችሁ የተነሣችሁት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ ነው፤ ለመሆኑ ታጒረመርሙበት ዘንድ አሮን ማነው?”

12. ከዚያም ሙሴ የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን አስጠራቸው፤ እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፤ “እኛ አንመጣም!

13. በምድረ በዳ ልትገድለን ማርና ወተት ከምታፈሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህም? አሁን ደግሞ በእኛ ላይ ጌታ መሆን ያምርሃል?

14. ከዚህም በቀር አንተ ማርና ወተት ወደምታፈሰው ምድር አላመጣኸንም፤ ወይም ዕርሻዎችንና የወይን ተክል ቦታዎች አላወረስከንም። ታዲያ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ታወጣለህን? በጭራሽ አንመጣም!”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 16