ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 17:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2. “ለእስራኤላውያን ንገራቸውና ከየነገዱ አለቆች አንዳንድ፣ ባጠቃላይ ዐሥራ ሁለት በትር ተቀበል፤ የያንዳንዱንም ሰው ስም በየበትሩ ላይ ጻፈው።

3. ለያንዳንዱ የነገድ አለቃ አንዳንድ በትር መኖር ስላለበት በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ።

4. በትሮቹንም እኔ ከአንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ ፊት ለፊት አስቀምጣቸው።

5. እኔ የምመርጠው ሰው በትርም ታቈጠቍጣለች፤ እስራኤላውያን በእናንተ ላይ ነጋ ጠባ የሚያደርጉትንም ማጒረምረም በዚህ እገታለሁ።

6. ሙሴም ለእስራኤላውያን ተናገራቸው፤ አለቆቻቸውም በቀደሙት በያንዳንዱ አባቶች ስም ዐሥራ ሁለት በትር ሰጡት፤ የአሮን በትርም በበትሮቹ መካከል ነበረች።

7. ሙሴም በትሮቹን ወስዶ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አኖራቸው።

8. በማግስቱ ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ሲገባ በሌዊ ቤት ስም የቀረበችው የአሮን በትር ማቈጥቈጥ ብቻ ሳይሆን እንቡጥ አውጥታ፣ አብባና ለውዝ አፍርታ አገኛት።

9. ከዚያም ሙሴ በትሮቹን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አውጥቶ ወደ እስራኤላውያን ሁሉ አመጣቸው፤ እነርሱም አዩ፤ እያንዳንዱም ሰው የየራሱን በትር ወሰደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 17