ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 24:8-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከግብፅ አወጣቸው፤ብርታታቸውም እንደ ጎሽ ብርታት ነው፤ጠላቶች የሆኑአቸውን ሕዝብ ያነክታሉ፤ዐጥንቶቻቸውን ያደቅቃሉ፤በፍላጾቻቸው ይወጓቸዋል።

9. እንደ አንበሳ አድፍጠዋል፤እንደ እንስቲቱም አንበሳ አድብተዋል፤ ሊቀሰቅሳቸውስ የሚችል ማን ነው?“የሚባርኩህ ቡሩክ፣የሚረግሙህም ርጉም ይሁኑ።”

10. ከዚያም ባላቅ፣ በበለዓም ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እጆቹንም አጨብጭቦ እንዲህ አለው፤ “ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፤ አንተ ግን ሦስቱንም ጊዜ ባረክሃቸው።

11. በል ቶሎ ወደ ቤትህ ሂድልኝ፤ ወሮታህን አሳምሬ ልከፍልህ ነበር፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን እንዳታገኝ ከለከለህ።”

12. በለዓምም ለባላቅ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ወደ እኔ ለላክሃቸው ሰዎች እንዲህ ብዬ ነግሬአቸው አልነበረምን?

13. ‘ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለውን ብቻ ከመናገር በስተቀር ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ውጭ በራሴ ሐሳብ በጎም ሆነ ክፉ ማድረግ አልችልም።’

14. እንግዲህ ወደ ሕዝቤ እመለሳለሁ፤ ይሁን እንጂ በሚመጣው ዘመን ይህ ሕዝብ በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውንና ልንገርህ።”

15. ከዚያም እንዲህ ሲል ንግሩን ጀመረ፤“የቢዖር ልጅ የበለዓም ንግር፤የዚያ ዐይኑ የተከፈተለት ሰው ንግር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 24