ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 30:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. “እንዲሁም ከተሳለች ወይም አምልጦአት ተናግራ ራሷን ግዴታ ውስጥ ካስገባች በኋላ ባል ብታገባ፣

7. ባሏም ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር ስእለቶቿ ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች መፈጸም ይኖርባቸዋል።

8. ሆኖም ባሏ ይህንኑ ሰምቶ ከከለከላት ግን ለመፈጸም የተሳለችውንም ሆነ አምልጦአት ተናግራ ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበትን ነገር ስለሚያስቀር እግዚአብሔር (ያህዌ) ከዚህ ነጻ ያደርጋታል።

9. “ባሏ የሞተባት ወይም ከባሏ የተፋታች ሴት የትኛውም ስእለቷ ወይም የገባችበት ግዴታ ሁሉ የጸና ይሆናል።

10. “ከባሏ ጋር የምትኖር ሴት ብትሳል ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሷን ግዴታ ውስጥ ብታስገባና

11. ባሏም ይህንኑ ሰምቶ ምንም ነገር ባይላትና ባይከለክላት ግን ስእለቶቿም ሆኑ ለማድረግ ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች ሁሉ የጸኑ ይሆናሉ።

12. ባሏ ሰምቶ እንዲቀሩ ካደረገ ግን ስእለቶቿንም ሆነ ለማድረግ ቃል የገባቻቸውን ነገሮች የመፈጸም ግዴታ የለባትም፤ ባሏ እንዲቀሩ ስላደረጋቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ነጻ ያደርጋታል።

13. የትኛውንም ስእለቷን ወይም ራሷን ለመከላከል በመሐላ የታሰረችበትን ሁሉ ባሏ ሊያጸናው ወይም ሊያፈርሰው ይችላል።

14. ይሁን እንጂ ባሏ ግን ስለ ጒዳዩ ከዕለት ወደ ዕለት ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር ስእለቶቿን ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸውን ነገሮች ሁሉ እያጸናላት ነው ማለት ነው፤ ስለ ነገሮቹ ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት በመቅረቱ አጽንቶላታል።

15. ስለ ነገሮቹ ከሰማ በኋላ እንዲቀሩ ካደረገ ግን ለፈጸመችው በደል በኀላፊነት የሚጠየቀው ራሱ ነው።”

16. እነዚህ እንግዲህ በባልና በሚስት፣ በአባትና አብራው በቤት ውስጥ በምትኖር ልጁ መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የሰጠው ሥርዐቶች ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 30