ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 34:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2. “እስራኤላውያንን እዘዛቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ወደምትካፈሏት ወደ ከነዓን ምድር በምትገቡበት ጊዜ አዋሳኞቿ እነዚህ ይሆናሉ፤

3. “ ‘የደቡብ ድንበራችሁ በኤዶም ወሰን ላይ ካለው ከጺን ምድረ በዳ ጥቂቱን ይጨምራል፤ በምሥራቅም በኩል የደቡብ ድንበራችሁ ከጨው ባሕር ጫፍ ይጀምርና

4. በአቅረቢም መተላለፊያ አቋርጦ እስከ ጺን ይሄድና በስተ ደቡብ እስከ ቃዴስ በርኔ ይዘልቃል፤ ከዚያም በሐጸር አዳር ዐልፎ እስከ ዓጽሞን ይደርስና

5. ዞሮ ከግብፅ ወንዝ ደረቅ መደብ ጋር በመገናኘት መጨረሻው ባሕሩ ይሆናል።

6. “ ‘የምዕራቡ ድንበራችሁ ደግሞ የታላቁ ባሕር ዳርቻ ይሆናል። በምዕራቡ በኩል ያለው ወሰናችሁም ይኸው ነው።

7. “ ‘የሰሜን ድንበራችሁን ከታላቁ ባሕር እስከ ሖር ተራራ ምልክት አድርጉበት፤

8. ከሖር ተራራ እስከ ሌቦ ሐማት እንደዚሁ አድርጉ፤ ከዚያም ወሰኑ እስከ ጽዳድ ይሄድና

9. እስከ ዚፍሮን በመቀጠል መጨረሻው ሐጻርዔናን ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ያለው ወሰናችሁ ይኸው ነው።

10. “ ‘ለምሥራቁ ድንበራችሁም እንደዚሁ ከሐጸርዔናን እስከ ሴፋማ ምልክት አድርጉበት።

11. ወሰኑም ከሴፋማ አንሥቶ ከዓይን በስተ ምሥራቅ እስካለው እስከ ሪብላ ቊልቊል ይወርድና ከኪኔሬት ባሕርሀ በስተ ምሥራቅ እስካሉት ሸንተረሮች ድረስ ይዘልቃል።

12. ከዚያም ወሰኑ የዮርዳኖስን ወንዝ ተከትሎ መጨረሻው የጨው ባሕር ይሆናል።“ ‘እንግዲህ በዙሪያዋ ካሉት ወሰኖቿ ጋር ምድራችሁ ይህች ናት።’ ”

13. ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “ይህችን ምድር ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ደልድሉ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለዘጠኙና ለግማሹ ነገድ እንድትሰጥ አዞአል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 34