ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 35:9-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

10. “እስራኤላውያንን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ወደ ከነዓን ለመግባት ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ጊዜ፣

11. ሳያስበው ሰው የገደለ ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ከተሞች እንዲሆኑ መማጸኛ ከተሞችን ምረጡ።

12. እነዚህም፣ ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ዘንድ ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት እንዳይሞት ከደም ተበቃዩ የሚሸሽባቸው የመማጸኛ ከተሞች ይሆናሉ።

13. እነዚህ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ስድስት ከተሞች መማጸኛ ከተሞቻችሁ ይሆናሉ።

14. ስለዚህ ከዮርዳኖስ ወዲህ ሦስቱን እንዲሁም በከነዓን ሦስቱን የመማጸኛ ከተሞች አድርጋችሁ ስጡ።

15. እነዚህም ስድስት ከተሞች ሳያስበው ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው እንዲሸሽባቸው ለእስራኤላውያን፣ ለመጻተኞችና በመካከላቸው ለሚኖር ለማንኛውም ሕዝብ የመማጸኛ ቦታዎች ይሆናሉ።

16. “ ‘አንድ ሰው ሌላውን እንዲሞት በብረት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል።

17. ወይም አንድ ሰው መግደል የሚችል ድንጋይ በእጁ ቢይዝና ሌላውን ሰው እንዲሞት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል።

18. ወይም አንድ ሰው መግደል የሚችል ዕንጨት በእጁ ቢይዝና ሌላውን ሰው እንዲሞት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል።

19. ደም መላሹም ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው፤ ባገኘውም ጊዜ ይግደለው።

20. አንድ ሰው አስቦበት ሌላውን በክፋት ገፍትሮ ቢጥለው ወይም እንዲሞት ሆን ብሎ አንዳች ነገር ቢወረውርበት

21. ወይም ደግሞ በጥላቻ ተነሣሥቶ በእጁ ቢመታውና ቢሞት፣ ያ ሰው በሞት ይቀጣል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም መላሹም ገዳዩን ባገኘው ጊዜ ይግደለው።

22. “ ‘ነገር ግን በጥላቻ ሳይሆን እንዲያው በድንገት አንዱ ሌላውን ገፍትሮ ቢጥለው ወይም ሳያስበው አንዳች ነገር ቢወረውርበት

23. ወይም መግደል የሚችል ድንጋይ ሳያይ ጥሎበት ቢሞት፣ ጠላቱ ስላልሆነና ሊጐዳውም አስቦ ያላደረገው ስለ ሆነ፣

24. ማኅበሩ በዚህ ሰውና በደመኛው መካከል በእነዚህ ደንቦች መሠረት ይፍረድ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 35