ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 4:12-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. “እንዲሁም በመቅደሱ ውስጥ ለአገልግሎት የሚሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን በመሸከሚያው ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት።

13. “ከናሱ መሠዊያ ላይ ዐመዱን ጠርገው ሐምራዊ ጨርቅ ያልብሱት፤

14. ከዚያም ለመሠዊያው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣ የእሳት ማንደጃዎቹን፣ ሜንጦዎቹን፣ የእሳት መጫሪያዎቹንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን በላዩ ላይ ያድርጉ፤ በእነዚህም ላይ የአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ አልብሰው መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

15. “አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና ዕቃዎቹን፣ ንዋየ ቅዱሳቱንም በሙሉ ሸፍነው ከጨረሱ በኋላ ሰፈሩ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ሲሆን፣ ቀዓታውያን ለመሸከም ይምጡ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅዱሳቱን መንካት የለባቸውም፤ ስለዚህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያሉትን እነዚህን ዕቃዎች የሚሸከሙ ቀዓታውያን ናቸው።

16. “የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት፣ ደስ የሚያሰኝ ሽታ ባለው ዕጣን፣ ዘወትር በሚቀርበው በእህል ቍርባንና በቅብዐ ዘይቱ ላይ ኀላፊነት ይኖረዋል፤ እንደዚሁም ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ መቅደሱንና ዕቃዎቹን ጭምር ይጠብቃል።”

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

18. “የቀዓት ጐሣዎች ከሌዋውያን ተለይተው እንዳይጠፉ፤

19. ወደ ንዋየ ቅዱሳቱ በሚቀርቡበትም ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ አንተ ይህን አድርግላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ወደ መቅደሱ ይግቡ፤ እያንዳንዱንም ሰው በየሥራው ላይ ይደልድሉት፤ ምን መሸከም እንዳለበትም ያስታውቁት።

20. ቀዓታውያን ግን ንዋየ ቅዱሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳን ለማየት አይግቡ፤ ቢገቡ ይሞታሉ።”

21. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

22. “ጌድሶናውያንንም በየቤተ ሰባቸውና በየጐሣቸው ቊጠራቸው፤

23. ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ወንዶች ሁሉ ቊጠር።

24. “የጌድሶናውያን የሥራና የሸክም አገልግሎታቸው ይህ ነው፤

25. እነርሱም የማደሪያውን መጋረጃዎች፣ የመገናኛውን ድንኳን፣ መደረቢያውንና በላዩ ላይ ያለውን የአቆስጣ ቍርበት፣ የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ መጋረጃዎች ይሸከሙ፤

26. እንዲሁም በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፣ ገመዶችና ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህም ያገልግሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 4