ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 4:23-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ወንዶች ሁሉ ቊጠር።

24. “የጌድሶናውያን የሥራና የሸክም አገልግሎታቸው ይህ ነው፤

25. እነርሱም የማደሪያውን መጋረጃዎች፣ የመገናኛውን ድንኳን፣ መደረቢያውንና በላዩ ላይ ያለውን የአቆስጣ ቍርበት፣ የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ መጋረጃዎች ይሸከሙ፤

26. እንዲሁም በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፣ ገመዶችና ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህም ያገልግሉ።

27. የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፣ ሸክምም ሆነ ሌላ ሥራ አሮንና ልጆቹ በሚሰጡት አመራር መሠረት ይሆናል። የሚሸከሙትን ሁሉ በኀላፊነት ታስረክቧቸዋላችሁ።

28. እንግዲህ የጌድሶናውያን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን የሚኖራቸው አገልግሎት ይህ ነው፤ ተግባራቸውም በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ይሆናል።

29. “ሜራሪያውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰቦቻቸው ቊጠራቸው፤

30. እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቊጠር።

31. በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎቶቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ተግባራቸው ይህ ነው፤ የማደሪያውን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎችንና መቆሚያ እግሮቻቸውን፣ ይሸከማሉ፤

32. እንደዚሁም በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ካስማዎችን፣ ገመዶችን፣ ከእነዚሁ ጋር ያሉትን ዕቃዎች ሁሉና ማንኛውም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚሸከመውን ዕቃ ለይታችሁ በስሙ መድቡለት።

33. እንግዲህ የሜራሪያውያን ጐሣዎች በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ሥር ሆነው በመገናኛው ድንኳን ሲሠሩ አገልግሎታቸው ይህ ነው።”

34. ሙሴ፣ አሮንና የማኅበረ ሰቡ አለቆች ቀዓታውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው።

35. ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት ሆኖአቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል የመጡት ወንዶች ሁሉ፣

36. በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 4