ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 8:11-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ከዚያም አሮን ሌዋውያኑን የእግዚአብሔርን (ያህዌ) አገልግሎት ለማከናወን ዝግጁ እንዲሆኑ ከእስራኤላውያን መካከል እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርባቸው።

12. “ሌዋውያኑ እጃቸውን በወይፈኖቹ ራስ ላይ ከጫኑ በኋላ ለሌዋውያኑ ማስተስረያ ይሆኑ ዘንድ የኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው።

13. ከዚያም ሌዋውያኑን በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው።

14. በዚህ መሠረት ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ትለያቸዋለህ፤ እነርሱም የእኔ ይሆናሉ።

15. “ሌዋውያኑን ካነጻሐቸውና እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህ ካቀረብሀቸው በኋላ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጣሉ፤

16. እነርሱም ሙሉ በሙሉ የእኔ እንዲሆኑ የተሰጡኝ እስራኤላውያን ናቸው፤ ከማንኛዪቱም እስራኤላዊት በተወለደ በኵር ወንድ ልጅ ምትክ የራሴ እንዲሆኑ ወስጃቸዋለሁ።

17. ከሰውም ሆነ ከእንስሳ በእስራኤል የተወለደ ማንኛውም በኵር ተባዕት የእኔ ነው፤ በግብፅ የነበረውን በኵር ሁሉ በመታሁ ጊዜ የእኔ እንዲሆኑ ለይቻቸዋለሁ።

18. በእስራኤል በተወለዱት ተባዕት በኵሮች ሁሉ ምትክም ሌዋውያኑን ወስጃለሁ።

19. እስራኤላውያንን ወክለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት እንዲያከናውኑና እስራኤላውያን ወደ ተቀደሰው ስፍራ ቢቀርቡ እንዳይቀሠፉ ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፣ ከእስራኤላውያን ሁሉ መካከል ሌዋውያኑን ስጦታ አድርጌ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻቸዋለሁ።”

20. ሙሴና አሮን እንዲሁም የእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት በሌዋውያኑ አደረጉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 8