ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 8:3-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት መብራቶቹ በመቅረዙ ላይ ሆነው ፊት ለፊት እንዲያበሩ አስቀመጣቸው።

4. የመቅረዙ አሠራር እንዲህ ነበር፤ ከመቆሚያው እስከ አበቦቹ ያለው ከተቀጠቀጠ ወርቅ የተሠራ ሲሆን፣ የመቅረዙም አሠራር እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ ባሳየው መሠረት ነበር።

5. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

6. “ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ለይተህ በሥርዐቱ መሠረት አንጻቸው።

7. ስታነጻቸውም እንዲህ አድርግ፤ በሚያነጻ ውሃ እርጫቸው፤ ገላቸውን በሙሉ ተላጭተው ልብሳቸውን ይጠቡ፤ በዚህም ይንጹ።

8. በዘይት ከተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን ጋር አንድ ወይፈን ይውሰዱ፤ ከዚያም ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን ሌላ ወይፈን አንተ ትወስዳለህ።

9. ሌዋውያኑን ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አምጣ፤ መላውንም የእስራኤል ማኅብረ ሰብ ሰብስብ፤

10. ሌዋውያኑን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቅርብ፤ ከዚያም እስራኤላውያን እጃቸውን ይጫኑባቸው።

11. ከዚያም አሮን ሌዋውያኑን የእግዚአብሔርን (ያህዌ) አገልግሎት ለማከናወን ዝግጁ እንዲሆኑ ከእስራኤላውያን መካከል እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርባቸው።

12. “ሌዋውያኑ እጃቸውን በወይፈኖቹ ራስ ላይ ከጫኑ በኋላ ለሌዋውያኑ ማስተስረያ ይሆኑ ዘንድ የኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው።

13. ከዚያም ሌዋውያኑን በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 8