ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 9:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ሙሴን፣ “በሬሳ ምክንያት ረክሰናል፤ ታዲያ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መሥዋዕት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ሆነን በተወሰነው ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?” አሉት።

8. ሙሴም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ የሚያዘውን እስካውቅ ድረስ ጠብቁ” ሲል መለሰላቸው።

9. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

10. “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከእናንተ ወይም ከዘሮቻችሁ ማንኛውም ሰው በሬሳ ምክንያት ቢረክስ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ፋሲካ ማክበር ይችላል፤

11. ይህንም በሁለተኛው ወር፣ በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ያክብሩ፤ የፋሲካውንም በግ እርሾ ከሌለበት ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።

12. እስኪነጋ ድረስ ከዚህ ምንም አያስተርፉ፤ ከዐጥንቱም ምንም አይስበሩ፤ ፋሲካን በሚያከብሩበት ጊዜ ሥርዐቱን በሙሉ መጠበቅ አለባቸው።

13. በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ የሆነ ወይም ሩቅ መንገድ ያልሄደ ሰው ፋሲካን ሳያከብር ቢቀር፣ ያ ሰው የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መሥዋዕት በተወሰነው ጊዜ አላቀረበምና ከወገኖቹ ፈጽሞ ይለይ፤ ያም ሰው የኀጢአቱን ዋጋ ይቀበላል።

14. “ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ፋሲካ ለማክበር ቢፈልግ በሕጉና በሥርዐቱ መሠረት መፈጸም አለበት፤ ለመጻተኛውም ሆነ ለአገሬው ተወላጅ የሚኖራችሁ ሕግ አንድ ይሁን።’ ”

15. ማደሪያው በተተከለ ዕለት ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ ማደሪያውን የሸፈነው ደመና እሳት ይመስል ነበር።

16. ይህ በዚህ ሁኔታ ቀጠለ፤ ደመናው ማደሪያውን ሸፈነው፤ በሌሊትም የእሳት መልክ ነበረው።

17. ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ እስራኤላውያን ጒዞአቸውን ይጀምሩ ነበር፤ ደመናው በሚቆምበት ቦታ ደግሞ ይሰፍሩ ነበር፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘኁልቍ 9