ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 12:33-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

33. ግብፃውያን አገራቸውን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡላቸው እስራኤላውያንን አጣደፏቸው። “አለበለዚያማ ሁላችንም ማለቃችን ነው” አሉ።

34. ስለዚህ ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሆ ዕቃው አድርገው በጨርቅ ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙ።

35. እስራኤላውያን ሙሴ እንዳዘዛቸው የብርና የወርቅ ዕቃዎች እንደዚሁም ልብስ እንዲሰጧቸው ግብፃውያኑን ጠየቋቸው።

36. እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያን ፊት ለእስራኤላውያን ሞገስ ስለሰጣቸው፣ የጠየቋቸውን ሁሉ ሰጧቸው፤ ስለዚህ የግብፃውያንን ንብረት በዝብዘው ወሰዱ።

37. እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከሴቶቹና ከልጆቹ ሌላ፣ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ወንዶች ነበሩ።

38. ከእነርሱም ጋር ቍጥሩ የበዛ ሌላ ድብልቅ ሕዝብ አብሮአቸው ወጣ፤ እንዲሁም አያሌ የበግ፣ የፍየል፣ የጋማና የቀንድ ከብት መንጋ ይዘው ወጡ።

39. ከግብፅ ይዘው ከወጡት ሊጥ ያልቦካ ቂጣ ጋገሩ፤ ሊጡ አልቦካም ነበር፤ ምክንያቱም ከግብፅ በጥድፊያ እንዲወጡ ስለተደረጉ፣ ለራሳቸው ምግብ ለማዘጋጀት ጊዜ አልነበራቸውም።

40. እንግዲህ እስራኤላውያን በግብፅ የኖሩበት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነበር።

41. ልክ አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመ ዕለት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰራዊት ሁሉ ግብፅን ለቆ ወጣ።

42. እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚያች ሌሊት እነርሱን ከግብፅ ለማውጣት ዘብ የቆመበት በመሆኑ፣ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ያከብሩ ዘንድ፣ በዚያች ሌሊት እስራኤላውያን ሁሉ ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል።

43. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “የፋሲካ በዓል አከባበር ሥርዐት እንዲህ ነው፤ ባዕድ የሆነ ሰው ከፋሲካው ምግብ አይብላ፤

44. በገንዘብ የገዛኸው ማንኛውም ባሪያ ከገረዝኸው በኋላ መብላት ይችላል፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 12