ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 24:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሙሴ የደሙን እኩሌታ ወስዶ በጎድጓዳ ሣህኖች አኖረው፤ የቀረውንም እኩሌታ በመሠዊያው ላይ ረጨው።

7. ከዚያም የኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ እንታዘዛለን” አሉ።

8. ከዚያም ሙሴ ደሙን ወሰደ፤ ሕዝቡም ላይ ረጭቶ፣ “ይህ እነዚህን ቃሎች በሰጠ ጊዜ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባው የቃል ኪዳኑ ደም ነው” አላቸው።

9. ሙሴና አሮን፣ ናዳብና አብድዩ እንደዚሁም ሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ወደ ተራራው ወጡ፣

10. የእስራኤልንም አምላክ (ኤሎሂም) አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ብሩህ ሰማይ የጠራ የሰንፔር ወለል ነበር።

11. ሆኖም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በእስራኤል ሕዝብ አለቆች ላይ እጁን አላነሣባቸውም። እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) አዩ፣ በሉ፤ ጠጡም።

12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በተራራው ላይ ወደ እኔ ና፤ በዚህም ቆይ፤ እኔም መመሪያ እንዲሆናቸው ሕግና ትእዛዛት የጻፍኩባቸውን የድንጋይ ጽላቶች እሰጥሃለሁ” አለው።

13. ከዚያም ሙሴ ከረዳቱ ከኢያሱ ጋር አብሮ ሄደ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ ወጣ።

14. እርሱም ሽማግሌዎችን “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩ፤ አሮንና ሖር ከእናንተ ጋር ናቸው፤ ክርክር ያለው ሰው ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ።” አላቸው።

15. ሙሴ ወደ ተራራ ሲወጣ ደመናው ተራራውን ሸፈነ፤

16. የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፣ ደመናውም ተራራውን እስከ ስድስት ቀን ድረስ ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ጠራው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 24