ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 29:19-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. “ሌላውን አውራ በግ ወስደህ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጭኑበታል።

20. አውራውንም በግ እረደው፤ ከደሙም ወስደህ የአሮንንና የወንዶች ልጆቹን የቀኝ ጆሮዎቻቸውን ጫፍ የቀኝ እጆቻቸውን አውራ ጣቶች፣ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣቶች ቅባቸው፤ ከዚያም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን እርጨው።

21. በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅብዐ ዘይቱ ወስደህ በአሮንና በልብሶቹ ላይ እንዲሁም በወንዶች ልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ እርጨው። ከዚያም እርሱና ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም ልብሶቻቸው የተቀደሱ ይሆናሉ።

22. ‘ከዚህ አውራ በግ ስቡን፣ ላቱን፣ በሆድ ዕቃው ውስጥ ያለውን ስብ፣ የጉበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና በዙሪያቸው ያለውን ስብና ቀኙን ወርች ውሰድ፤ ይህ የክህነት አውራ በግ ነው።

23. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በሌማት ካለው ያለ እርሾ ከተጋገረው ቂጣ፣ ዳቦ፣ በዘይት የተሠራ እንጎቻና ኅብስት ውሰድ።

24. እነዚህን ሁሉ በአሮንና በወንዶች ልጆቹ እጆች ላይ በማኖር እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዝውዛቸው።

25. ከዚያም ከእጃቸው ወስደህ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መልካም መዓዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

26. ለአሮን ክህነት የአውራ በጉን ፍርምባ ከወሰድህ በኋላ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዝውዘው ይህም የአንተ ድርሻ ይሆናል።

27. “ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ለክህነት የሆኑትን የአውራውን በግ ብልቶች፣ ቀድሳቸው። የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች

28. ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የዘወትር የእስራኤላውያን ድርሻ የሚሆነው ይህ ነው፤ ከኅብረት መሥዋዕታቸው እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡት ነው።

29. “የአሮን የተቀደሱ ልብሶች ለትውልዶቹ ይሆናሉ፤ ይኸውም በእነርሱ ይቀቡና ክህነትን ይቀበሉ ዘንድ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 29