ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 36:3-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ለማከናወን እስራኤላውያን ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ተቀበሉ፤ ሕዝቡ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን በየማለዳው ማምጣታቸውን ቀጠሉ።

4. ስለዚህ የመቅደሱን ሥራ ሁሉ ይሠሩ የነበሩ ጥበበኞች የሆኑ ባለ ሙያዎች ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፤

5. ሙሴንም፣ “ሕዝቡ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ እያመጡ ነው” አሉት።

6. ከዚያም ሙሴ ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህንንም ቃል ወደ ሰፈሩ ላኩት፤ “ማንም ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ሌላ ምንም ስጦታ ማድረግ የለበትም፤” ስለዚህ ሕዝቡ ትርፍ እንዳያመጡ ተከለከሉ፤

7. ምክንያቱም ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በእጃቸው ያለው ከበቂ በላይ ነበረ።

8. የሥራ ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የማደሪያውን ድንኳን በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በጥልፍ ዐዋቂ፣ ኪሩቤል ከተጠለፉበት ከዐሥር መጋረጃዎች ሠሩት።

9. መጋረጃዎቹም ሁሉ ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ሲሆን፣ ቁመታቸው ሃያ ስምንት ክንድ፣ ወርዳቸው አራት ክንድ ነበር።

10. አምስቱን መጋረጃዎች ባንድ ላይ በማጋጠም ሰፏቸው፤ የቀሩትን አምስቱንም እንዲሁ አደረጉ።

11. ተጋጥሞ ከተሰፋው መጋረጃ ጠርዝ ጫፍ ላይ ከሰማያዊ ግምጃ ቀለበቶችን አበጁ፤ ተጋጥሞ በተሰፋው በሌላው መጋረጃ ጫፍ ላይም ተመሳሳይ ነገር አደረጉ።

12. በአንደኛው መጋረጃ ላይ አምሳ ቀለበቶችን በሌላው ተጋጥሞ ከተሰፋው በስተ መጨረሻ ካለው መጋረጃ ላይ አምሳ ቀለበቶችን እርስ በርሳቸው ትይዩ በማድረግ ሠሩት።

13. ከዚያም አምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሠሩ፤ የማደሪያው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድም ተጋጥመው የተሰፉትን ሁለቱን መጋረጃዎች አያያዙባቸው።

14. ከማደሪያው በላይ ለሚሆነው ድንኳን ከፍየል ቆዳ የተሠሩ በጠቅላላ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ሠሩ።

15. ዐሥራ አንዱ መጋረጃዎች ተመሳሳይ ልክ ሲኖራቸው፣ ቁመታቸው ሠላሳ ክንድ፣ ወርዳቸውም አራት ክንድ ነበር።

16. አምስቱን መጋረጃዎች በአንድ በኩል፣ ሌሎቹን ስድስት መጋረጃዎች ደግሞ በሌላ በኩል አንድ ላይ አያያዟቸው።

17. በስተ መጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን፣ በሌላ በኩል ባለው በስተ መጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ አምሳ ቀለበቶችን አበጁ።

18. ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝም አምሳ የናስ ማያያዣዎችን ሠሩ።

19. ከዚያም ለድንኳኑ መሸፈኛ የሚሆን ቀይ ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ሠሩ፤ በላዩ ላይ የሚሆንም የአቆስጣ ቆዳ አበጁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 36