ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 39:25-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ከንጹሕ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፤ እነዚህንም በሮማኖቹ መካከል በጠርዙ ዙሪያ አደረጉ።

26. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ለአገልግሎት ይለበሱ ዘንድ ሻኵራዎቹና ሮማኖቹ በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ላይ ተሰባጥረው ይገኙ ነበር።

27. ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የሸማኔ ሥራ የሆነውን ከቀጭን በፍታ ሸሚዞችን ሠሩ፤

28. እንዲሁም ከቀጭን በፍታ ጥምጥምን፣ የሐር ቆቦቹንና በቀጭኑ ከተፈተለም በፍታ ሱሪዎችን ሠሩ።

29. መታጠቂያው እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ የጥልፍ ጠላፊ ሥራ ሆኖ የተሠራ ነበረ።

30. ከንጹሕ ወርቅ የተቀደሰውን አክሊል ሰሌዳ ሠርተው፣ በማኅተም ላይ እንደ ተቀረጸ ጽሑፍ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር (ያህዌ)” የሚል ቀረጹበት፤

31. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ከመጠምጠሚያው ጋር ለማያያዝ ሰማያዊ ፈትል አሠሩበት።

32. በዚህ መሠረት የማደሪያው ድንኳን፣ የመገናኛው ድንኳን ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ እስራኤላውያን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉን ነገር ሠሩ።

33. ከዚያም የማደሪያውን ድንኳን ወደ ሙሴ አመጡት፤ እነዚህም ድንኳንና ዕቃዎቹ ሁሉ፣ ማያያዣዎቹ፣ ክፈፎቹ፣ አግዳሚዎቹ፣ ምሰሶዎቹና መቆሚያዎቹ፤

34. ቀይ ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ የተሠራ መደረቢያ፣ የለፋ የአቆስጣ ቆዳ መደረቢያና መከለያ መጋረጃ፤

35. የምስክሩ ታቦት፣ ከመሎጊያዎቹና ከስርየት መክደኛው ጋር፤

36. ጠረጴዛው ከዕቃዎቹ ሁሉና ከኅብስተ ገጹ ጋር፤

37. ከንጹሕ ወርቅ የሆነው መቅረዝ ከተደረደሩት መብራቶችና ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋር፣ የመብራቱም ዘይት፣

38. የወርቅ መሠዊያው፣ ቅብዐ ዘይቱ፣ መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን እንዲሁም የድንኳኑ መግቢያ መጋረጃ፣

39. የናስ መሠዊያው ከናስ መጫሪያው፣ መሎጊያዎቹና ዕቃዎቹ ሁሉ ጋር፤ የመታጠቢያው ሳሕን ከነማስቀመጫው፣

40. የአደባባዩ መጋረጃዎች ከምሰሶዎቹና ከመቆሚያዎቹ ጋር፣ የአደባባዩ መግቢያ መጋረጃ፣ ገመዶቹና የአደባባዩ ድንኳን ካስማዎች፣ የማደሪያው የመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች ሁሉ፤

41. በመቅደሱ ሲያገለግሉ የሚለበሱት የተፈተሉት ቀሚሶች፣ ለካህኑ ለአሮን የተቀደሱት ቀሚሶችና ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚያደርጓቸው ቀሚሶች ናቸው።

42. እስራኤላውያን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ሥራውን ሁሉ አከናወኑ።

43. ሙሴ ሥራውን አየ፤ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው መሥራታቸውንም ተመለከተ፤ ስለዚህ ባረካቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 39