ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 19:14-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ሎጥ ከቤቱ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኞች የሆኑትን ዐማቾቹን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህችን ከተማ ሊያጠፋት ነውና በፍጥነት ከዚህ ስፍራ ውጡ” አላቸው፤ ዐማቾቹ ግን የሚቀልድ መሰላቸው።

15. ሲነጋጋም መላእክቱ ሎጥን፣ “ከከተማዪቱ ጋር አብራችሁ እንዳትጠፉ፣ ሚስትህንና ሁለቱን ሴት ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ቦታ በፍጥነት ውጣ” ብለው አቻኰሉት።

16. ሎጥ ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ራራላቸው ሰዎቹ የእርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዪቱ በደኅና አወጧቸው።

17. እንዳወጧቸውም፣ መልአኩ፣ “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ፈጥናችሁ ሽሹ፤ መለስ ብላችሁ ወደ ኋላችሁ አትመልከቱ፤ ከረባዳው ስፍራ እንኳ ቆም አትበሉ፤ ወደ ተራራው ሽሹ፤ አለበለዚያ ትጠፋላችሁ” አላቸው።

18. ሎጥም እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንደዚህስ አይሁን፤

19. እነሆ፤ እኔ ባሪያህ አንዴ በፊትህ ሞገስ አግኝቻለሁ፤ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርኅራኄ አድርገህልኛል፤ እኔ እንደሆንሁ ወደ ተራሮቹ ሸሽቼ ማምለጥ ስለማልችል የሚወርደው መዓት ደርሶ ያጠፋኛል።

20. እነሆ፤ ወደዚያ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ የሆነች ትንሽ ከተማ አለች፤ ወደ እርሷ ልሽሽ፤ በጣም ትንሽ አይደለችም እንዴ? ወደዚያ ብሸሽ እኮ ሕይወቴ ትተርፋለች።”

21. እርሱም እንዲህ አለው፤ “ይሁን እሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ፤ ያልካትንም ከተማ አላጠፋትም።

22. አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ አንዳች ማድረግ ስለማልችል ቶሎ ብለህ ወደዚያ ሽሽ” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 19