ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 24:17-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት።

18. እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው።

19. እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች።

20. ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጒድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው።

21. አገልጋዩም አንዲት ቃል ሳይናገራት፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) መንገዱን አሳክቶለት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ልጂቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር።

22. ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውዬው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣

23. “ለመሆኑ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኝ እንደሆነ፣ እባክሽ ንገሪኝ” ብሎ ጠየቃት።

24. እርሷም፣ “እኔ፣ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችው፤

25. ደግሞም፣ “በቤታችን በቂ ገለባና ድርቈሽ እንዲሁም ለእናንተ የሚሆን ማደሪያ አለን” አለችው።

26. ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገደ፤

27. እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የተመሰገነ ይሁን።”

28. ልጂቷ ሮጣ ሄዳ፣ የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተ ሰቦች ነገረች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 24