ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 24:2-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ፣ የቤቱ ሁሉ አዛዥ የሆነውን አረጋዊ አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፤

3. ልጄን፣ በመካከላቸው ከምኖር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋር እንዳታጋባው በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ማልልኝ።

4. ነገር ግን ወደ አገሬ፣ ወደ ገዛ ዘመዶቼ ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት ትፈልግለታለህ።”

5. አገልጋዩም፣ “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ምን አደርጋለሁ? ልጅህን አንተ ወደ መጣህበት አገር ልውሰደውን?” ሲል ጠየቀው።

6. አብርሃምም እንዲህ አለው፤ “ምንም ቢሆን ልጄን ወደዚያ እንዳትመልሰው ተጠንቀቅ፤

7. ከአባቴ ቤት፣ ከትውልድ አገሬ ያወጣኝና፣ ‘ለዘርህ ይህችን ምድር እሰጣለሁ’ ብሎ በመሐላ ተስፋ የገባልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤ ለልጄም ሚስት ከዚያ ታመጣለታለህ።

8. ሴቲቱ አብራህ ወደዚህ ለመምጣት ፈቃደኛ ካልሆነች ግን ካስማልሁህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትውሰደው” አለው።

9. ስለዚህም አገልጋዩ እጁን ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች አድርጐ ስለዚህ ጒዳይ ማለለት።

10. አገልጋዩም ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥሩን ወሰደ፤ ምርጥ ምርጡንም ዕቃ ሁሉ ጭኖ፣ የናኮር ከተማ ወደምትገኝበት ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ተጓዙ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 24