ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 24:38-50 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

38. ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት፣ ወደ ገዛ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት አምጣለት’።

39. “እኔም ጌታዬን፣ ‘ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ለመምጣት ባትፈቅድስ?’ ብዬ ጠየቅሁት።

40. “እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፤ ከገዛ ወገኖቼና ከአባቴ ቤት፣ ለልጄ ሚስት እንድታመጣለት መንገድህን ያቃናል።

41. ወደ ወገኖቼ ከሄድህ፣ ከመሐላው የተፈታህ ትሆናለህ፤ እነርሱ እንኳ ልጂቱን አንሰጥም ቢሉህ፣ ከመሐላው ንጹሕ ትሆናለህ’ አለኝ።

42. “እኔም ዛሬ ወደ ውሃው ጒድጓድ ስደርስ እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሆይ፤ ፈቃድህ ቢሆን የመጣሁበትን ጒዳይ አቃናልኝ፤

43. እነሆ፤ በምንጩ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ ውሃ ልትቀዳ የምትመጣውን ኮረዳ፣ “ከእንስራሽ ውሃ አጠጪኝ” ስላት፣

44. እሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ” የምትለኝ እርሷ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለጌታዬ ልጅ የመረጣት ትሁን።’

45. “በልቤ የምጸልየውን ጸሎት ገና ሳልጨርስ፣ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች፤ ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ ቀዳች። እኔም፣ ‘እባክሽ፤ ውሃ አጠጪኝ’ አልኋት።

46. “እርሷም ፈጥና እንስራዋን ከትከሸዋ አውርዳ፣ ‘ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣለሁ’ አለች። እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቹንም አጠጣች።

47. “ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ” ብዬ ጠየቅኋት።“እርሷም፣ ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለችኝ።“ከዚያም ቀለበቱን አደረግሁላት፤ አምባሩንም በእጇ አስገባሁላት።

48. ተደፍቼም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገድሁ፤ ለጌታዬ ወንድም የልጅ ልጅ የሆነችውን ቈንጆ፣ ለጌታዬ ልጅ እንዳገኝለት በቀና መንገድ የመራኝ የጌታዬ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አመሰገንሁ።

49. እንግዲህ አሁን ለጌታዬ በጎነትና ታማኝነት የምታሳዩ ከሆነ ሐሳባችሁን አስታውቁኝ፤ ካልሆነ ግን ቍርጡን ንገሩኝና የምሄድበትን ልወስን።”

50. ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ነገሩ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ሆነ በዚህም ሆነ በዚያ ምንም ማለት አንችልም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 24