ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 26:12-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባረከለትና በዚያኑ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ።

13. ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ።

14. ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት።

15. ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሩአቸውን የውሃ ጒድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኑዋቸው።

16. አቢሜሌክም ይስሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው።

17. ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ።

18. ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኑአቸውን የውሃ ጒድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው።

19. የይስሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጒድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ።

20. የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይስሐቅ ያን የውሃ ጒድጓድ ኤሴቅ ብሎ ጠራው፤ በጒድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና።

21. አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጒድጓዱን ስጥና ብሎ ጠራው።

22. ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጒድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጒድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት ብሎ ጠራው።

23. ከዚያም ይስሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ።

24. በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው።

25. ይስሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 26