ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 29:15-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ላባ ያዕቆብን፣ “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለን አይገባምና ደመወዝህ ምንድን ነው?” አለው።

16. ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር።

17. ልያ ዐይነ ልም ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር።

18. ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው።

19. ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው።

20. ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ አጥብቆ ይወዳትም ስለ ነበረ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው።

21. ከዚያም ያዕቆብ ላባን፣ “እነሆ፤ የተባባልነው ጊዜ አብቅቶአል፤ ስለዚህ ሚስቴን አስረክበኝና የባልና የሚስት ወጋችንን እናድርስ” አለው።

22. ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ ሰርግ አበላ።

23. ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም አብሮአት ተኛ።

24. ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጡር እንድትሆን ሰጣት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 29