ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 30:36-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

36. ከዚያም በእርሱና በያዕቆብ መካከል የሦስት ቀን መንገድ ርቀት እንዲኖር አደረገ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጎች ማገዱን ቀጠለ።

37. ነገር ግን ያዕቆብ እርጥብ የልብን፣ የለውዝንና የኤርሞን በትሮች ወሰደ፤ ቅርፊታቸውንም በቀጭን ልጦ እያነሣ የበትሮቹ ግንድ ነጩ እንዲታይ፣ ሽመልመሌ መልክ እንዲኖራቸው አደረገ።

38. የላጣቸውንም በትሮች መንጎቹ ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ ከፊት ለፊት እንዲያዩአቸው በማጠጫ ገንዳዎቹ ሁሉ አስቀመጠ። መንጎቹም ስሜታቸው ሲነሣሣና ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ፣

39. በትሮቹን ፊት ለፊት እያዩ ይሳረሩ ነበር፤ ሽመልመሌ፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ የጣለባቸውንም ግልገሎች ወለዱ።

40. ያዕቆብ ግልገሎቹን ለብቻ ለያቸው፤ የቀሩትንም የላባ መንጎች ሽመል መሌና ጥቋቁር በሆኑት ትይዩ አቆማቸው፤ በዚህም መሠረት የራሱ መንጋ ከላባ መንጋ ጋር እንዳይቀላቀል ለብቻ ለየ።

41. ያዕቆብም ብርቱ እንስቶች አውራ ፈልገው በሚቅበጠ በጡበት ጊዜ፣ በትሮቹ አቅራቢያ እንዲጠቁ በትሮቹን በውሃ ገንዳዎቹ ውስጥ ፊት ለፊታቸው ያስቀምጥ ነበር፤

42. ደካማ በሆኑት እንስቶች ፊት ግን፣ በትሮቹን አያስቀምጥም ነበር፤ ስለዚህ ደካማ ደካማዎቹ ለላባ ሲሆኑ፣ ብርቱ ብርቱዎቹ ለያዕቆብ ሆኑ።

43. በዚህም ሁኔታ ይህ ሰው እጅግ ባለጠጋ ሆነ፤ የብዙ መንጎች፣ የሴትና የወንድ አገልጋዮች፣ እንዲሁም የግመሎችና የአህዮች ባለቤት ሆነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 30