ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 31:35-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. ራሔልም አባቷን፣ “በፊትህ ተነሥቼ መቆም ስላልቻልሁ፣ ጌታዬ አትቈጣ፤ የወር አበባዬ መጥቶ ነው።” አለችው፤ ስለዚህ በረበረ፤ የጣዖታቱን ምስል ግን ማግኘት አልቻለም።

36. በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ተቈጣ፤ ላባንም እንዲህ ሲል ወቀሰው፤ “እስቲ ወንጀሌ ምንድን ነው? ይህን ያህል የምታሳድደኝ ኀጢአቴ ምን ቢሆን ነው?

37. ዕቃዬን አንድ በአንድ በርብረሃል፤ ታዲያ፣ የአንተ ሆኖ ያገኘኸው ዕቃ የትኛው ነው? ካለ፣ እስቲ በአንተም በእኔም ዘመዶች ፊት አቅርብና እነርሱ ያፋርዱን።

38. ሃያ ዓመት አብሬህ ኖሬአለሁ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከመንጋህ አንድ ጠቦት እንኳ አልበላሁም።

39. አውሬ የሰበረውንም ቢሆን እተካ ነበር እንጂ፣ ትራፊውን ለምልክትነት አምጥቼ አላውቅም፤ በቀንም ሆነ በሌሊት የተሰረቁትን ሁሉ ስታስከፍለኝ ኖረሃል።

40. ቀን በሐሩር ሌሊት በቊር ተቃጠልሁ፤ እንቅልፍም በዐይኔ አልዞር አለ፤

41. ሃያ ዓመት በቤትህ የኖርሁት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ዐሥራ አራት ዓመት ለሁለቱ ልጆችህ ብዬ አገለገልሁ፤ ስድስት ዓመት ስለ መንጋዎችህ ስል አገለገልሁ፤ ይህም ሆኖ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ ለዋውጠኽብኛል።

42. የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም)፣ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም)፣ የይስሐቅም ፍርሀት ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ሰድደኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን መከራዬን አይቶ፣ ልፋቴን ተመልክቶ ትናንት ሌሊት ገሠጸህ።”

43. ላባም ለያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሴቶቹም፣ ልጆቹም የእኔው ልጆች ናቸው፣ መንጎቹም ቢሆኑ የራሴ ናቸው። ታዲያ፣ በእነዚህ ሴቶች ልጆቼና በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ ዛሬ ምን ማድረግ እችላለሁ?

44. በል አሁን ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ኪዳኑም በአንተና በእኔ መካከል ምስክር ይሁን።”

45. ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፤

46. ከዚያም ዘመዶቹን፣ “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ፤ በክምሩም አጠገብ ምግብ በሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 31