ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 32:8-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. “ዔሳው መጥቶ በአንደኛው ላይ አደጋ ቢጥል፣ ሌላው ክፍል ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ አስቦ ነበር።

9. ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ፣ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) ሆይ፤ ‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም በጎ ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤

10. እኔ ባሪያህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በስተቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሰራዊት ሆኛለሁ።

11. ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ መጥቶ እኔንም ሆነ እነዚህን እናቶች ከነልጆቻቸው ያጠፋናል ብዬ ፈርቻለሁና፤

12. ነገር ግን፣ አንተ ራስህ፣ ‘አበለጽግሃለሁ፤ ዘርህንም ሊቈጠር እንደማይቻል እንደ ባሕር አሸዋ አበዛዋለሁ’ ብለኸኛል።”

13. በዚያችም ሌሊት ያዕቆብ እዚያው አደረ፤ ካለው ሀብት ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻ እነዚህን መረጠ፦

14. ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችና ሃያ አውራ ፍየሎች፣ ሁለት መቶ እንስት በጎችና ሃያ አውራ በጎች፣

15. ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፣ አርባ ላሞችና ዐሥር ኮርማዎች፣ ሃያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባት አህዮች።

16. እነዚህንም በየመንጋው ለይቶ፣ የሚነዱአቸውን ጠባቂዎች መደበላቸው፤ ጠባቂዎቹንም፣ “እናንተ ቀድማችሁኝ ሂዱ፣ መንጋዎቹንም አራርቃችሁ ንዱአቸው” አላቸው።

17. ቀድሞ የሚሄደውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ዔሳው አግኝቶህ፣ ‘የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? የምትነዳውስ ይህ ሁሉ ከብት የማን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣

18. ‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደዳቸው ናቸው፤ እርሱም ከበስተ ኋላችን እየመጣ ነው’ ብለህ ንገረው፣”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 32