ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 9:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤

2. አስፈሪነታችሁና አስደንጋ ጭነታችሁ፦ በዱር አራዊት፣ በሰማይ አዕዋፍ፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች ሁሉ ላይ ይሁን፤ በእጃችሁ ተሰጥተዋል።

3. ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ።

4. “ነገር ግን ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ።

5. ሰውን የገደለ ሁሉ ስለሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ፣ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ።

6. “የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ፣ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል፤በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) አምሳል፣እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን ሠርቶታልና።

7. እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ፤ ይንሠራፋ።”

8. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና አብረውት ያሉትን ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤

9. “እነሆ፤ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤

10. እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ከወፎች፣ ከቤት እንሰሳት፣ ከዱር እንስሳት፣ ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ።

11. ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ።”

12. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ በእኔና በእናንተ መካከል፣ ከእናንተም ጋር ካሉ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ከሚመጣውም ትውልድ ሁሉ ጋር፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤

13. ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል።

14. ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፣

15. ከእናንተና ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን አስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም።

16. ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ፣ በእኔና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጡራን መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን አስባለሁ።”

17. ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን፣ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው” አለው።

18. ከመርከቧ የወጡትም የኖኅ ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ነበሩ፤ ካም የከነዓን አባት ነው።

19. ሦስቱ የኖኅ ልጆች እነዚህ ሲሆኑ፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የተገኙት ከእነዚሁ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 9