ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 14:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ፍቅርን ተከታተሉ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን፣ በተለይም ትንቢት የመናገርን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ።

2. በልሳን የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርምና፤ ምስጢር የሆነውን በመንፈስ ስለ ሚናገር የሚረዳው የለም።

3. ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰው ይናገራል።

4. በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል።

5. ሁላችሁም በልሳን ብትናገሩ እወዳለሁ፤ ከዚህ ይልቅ ግን ትንቢትን ብትናገሩ እወዳለሁ። ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ በልሳን የሚናገር ሰው የተናገረውን ካልተረጐመ፣ በልሳን ከሚናገር ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።

6. እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ በመግለጥ ወይም በዕውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ በልሳን ብናገር ምን እጠቅማችኋለሁ?

7. እንደ ዋሽንትና እንደ በገና ያሉ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች እንኳ የድምፃቸው ቃና ልዩነት ከሌለው ዜማቸውን እንዴት ማወቅ ይቻላል?

8. ደግሞም መለከት ትክክል ያልሆነ የጥሪ ድምፅ ካሰማ፣ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?

9. እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ ከአንደበታችሁ ትርጒም ያለው ቃል ካልወጣ፣ የምትናገሩትን ማን ሊያስተውለው ይችላል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 14