ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 4:10-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እኛ ስለ ክርስቶስ ብለን ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጥበበኞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን።

11. እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፤ እንጠማለን፤ እንራቈታለን፤ እንደ በደባለን፤ ያለ መጠለያ እንንከራተታለን፤

12. በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን። ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤

13. ስማችንን ሲያጠፉ መልካም እንመልሳለን። እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጒድፍ፣ የምድር ጥራጊ ሆነናል።

14. ይህን የምጽፍላችሁ እንደ ተወደዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልመክራችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ብዬ አይደለም።

15. ምንም እንኳ በዐሥር ሺህ የሚቈጠሩ ሞግዚቶች በክርስቶስ ቢኖሯችሁም፣ ብዙ አባቶች ግን የሏችሁም፤ በወንጌል አማካይነት በክርስቶስ ኢየሱስ ወልጄአችኋለሁና።

16. ስለዚህ እኔን እንድትመስሉ እለምናችኋለሁ።

17. እንግዲህ በጌታ የተወደደውንና የታመነውን ልጄን ጢሞቴዎስን የላክሁላችሁ በዚህ ምክንያት ነው፤ እርሱም በየስፍራው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከማስተምረው ትምህርት ጋር የሚስማማውን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን የሕይወት አካሄዴን ያሳስባችኋል።

18. ከእናንተ አንዳንዶቹ ወደ እናንተ የማልመጣ መስሎአቸው ታብየዋል፤

19. ይሁን እንጂ የጌታ ፈቃድ ቢሆን ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ ከዚያም እነዚህ ትዕቢተኞች የሚናገሩትን ብቻ ሳይሆን፣ ምን ኀይል እንዳላቸውም ማየት እሻለሁ።

20. ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት የወሬ ጒዳይ ሳይሆን የኀይል ጒዳይ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 4