ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 5:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በመካከላችሁ የዝሙት ርኵሰት እንዳለ በርግጥ ይወራል፤ እንዲህ ያለው ርኵሰት በአረማውያን ዘንድ እንኳ ታይቶ የማይታወቅ ነው፤ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው አለና።

2. ደግሞም ታብያችኋል! ይልቅስ ሐዘን ተሰምቶአችሁ፣ ይህን ድርጊት የፈጸመውን ሰው ከመካከላችሁ ልታስወግዱት አይገባምን?

3. ምንም እንኳ እኔ በአካል አብሬያችሁ ባልሆንም፣ በመንፈስ ግን ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ልክ አብሬያችሁ እንዳለሁ ሆኜ፣ ይህን ባደረገው ሰው ላይ አሁኑኑ ፈርጄበታለሁ።

4. በምትሰበሰቡበት ጊዜ እኔም በመንፈስ ከእናንተ ጋር ስለ ምሆን፣ በጌታችን በኢየሱስ ስምና በመካከላችሁ በሚገኘው በጌታችን በኢየሱስ ኀይል፣

5. ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ለሰይጣን ይሰጥ።

6. መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ብዙውን ሊጥ እንደሚያቦካው አታውቁምን?

7. አሁን ያለ እርሾ እንደሆናችሁ ሁሉ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ የፋሲካ በጋችን የሆነው ክርስቶስ ተሠውቶአልና።

8. ስለዚህ በዓሉን ግፍና ክፋት በሞላበት እርሾ፣ በአሮጌ እርሾ ሳይሆን፣ እርሾ በሌለበት ቂጣ በቅንነትና በእውነት እናክብር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 5