ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጴጥሮስ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በባልና በሚስት መካከል ሊኖር የሚገባ ግንኙነት

1. ሚስቶች ሆይ፤ እናንተም እንደዚሁ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤

2. ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው።

3. ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በመሽሞንሞን ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ በወርቅ በማጌጥና በልብስ አይሁን፤

4. ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን።

5. ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ላይ የጣሉ የቀድሞ ቅዱሳት ሴቶች ራሳቸውን ያስዋቡት በዚህ ዐይነት ለባሎቻቸው በመገዛት ነበርና።

6. ሣራም አብርሃምን “ጌታዬ” እያለች ትታዘዘው ነበር፣ እናንተም ምንም ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ የእርሷ ልጆች ናችሁ።

7. ባሎች ሆይ፤ እናንተም ደግሞ ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ በኑሮአችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ አስቡላቸው፣ ደካሞች ስለሆኑና የሕይወትንም በረከት አብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው።

መልካም በማድረግ መከራን መቀበል

8. በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩችና ትሑታን ሁኑ።

9. ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው።

10. ስለዚህ፣“ሕይወትን የሚወድ፣መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣ምላሱን ከክፉ፣ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል።

11. ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤

12. ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።”

13. መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው?

14. ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።”

15. ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤

16. በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ።

17. የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤

18. እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤

19. በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤

20. እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እምቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ።

21. ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤

22. እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።