ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 16:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም።

11. እንግዲህ፣ በዚህ ዓለም ሀብት ካልታመናችሁ፣ እውነተኛው ንማ ሀብት ማን ዐደራ ብሎ ይሰጣችኋል?

12. በሌላው ሰው ሀብት ካልታመናችሁ፣ የራሳችሁ የሆነውን ሀብት ማን ይሰጣችኋል?

13. “በአንድ ጊዜ ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም ባሪያ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን ይጠጋል፤ ሌላውን ይንቃል። የእግዚአብሔርም የገንዘብም ባሪያ መሆን አትችሉም።”

14. ገንዘብ የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው በኢየሱስ አፌዙበት።

15. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ በሰዎች ፊት ራሳችሁን የምታጸድቁ ናችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ልባችሁን ያውቃል፤ በሰዎች ዘንድ የከበረ፣ በእግዚአብሔር ፊት የረከሰ ነውና።

16. “ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ኖረዋል፤ ከዚያ በኋላ ግን የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ተሰብኮአል፤ ሰውም ሁሉ ወደዚያ ለመግባት ይሻማል።

17. ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል።

18. “ሚስቱን ፈቶ ሌላይቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ከባሏ የተፋታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”

19. ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ሐምራዊና ቀጭን በፍታ የለበሰ፣ በየቀኑም በተድላ ደስታ የሚኖር አንድ ሀብታም ሰው ነበረ።

20. በአንጻሩም፣ መላ ሰውነቱ በቊስል የተወረረ አንድ አልዓዛር የሚባል ድኻ በዚህ ሀብታም ሰው ደጃፍ ይተኛ ነበር፤

21. ከሀብታሙ ሰው ማእድ የወደቀውን ፍርፋሪ እንኳ ሊመገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾችም ሳይቀሩ መጥተው ቊስሉን ይልሱ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 16