ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 16:13-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. “በአንድ ጊዜ ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም ባሪያ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን ይጠጋል፤ ሌላውን ይንቃል። የእግዚአብሔርም የገንዘብም ባሪያ መሆን አትችሉም።”

14. ገንዘብ የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው በኢየሱስ አፌዙበት።

15. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ በሰዎች ፊት ራሳችሁን የምታጸድቁ ናችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ልባችሁን ያውቃል፤ በሰዎች ዘንድ የከበረ፣ በእግዚአብሔር ፊት የረከሰ ነውና።

16. “ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ኖረዋል፤ ከዚያ በኋላ ግን የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ተሰብኮአል፤ ሰውም ሁሉ ወደዚያ ለመግባት ይሻማል።

17. ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል።

18. “ሚስቱን ፈቶ ሌላይቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ከባሏ የተፋታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”

19. ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ሐምራዊና ቀጭን በፍታ የለበሰ፣ በየቀኑም በተድላ ደስታ የሚኖር አንድ ሀብታም ሰው ነበረ።

20. በአንጻሩም፣ መላ ሰውነቱ በቊስል የተወረረ አንድ አልዓዛር የሚባል ድኻ በዚህ ሀብታም ሰው ደጃፍ ይተኛ ነበር፤

21. ከሀብታሙ ሰው ማእድ የወደቀውን ፍርፋሪ እንኳ ሊመገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾችም ሳይቀሩ መጥተው ቊስሉን ይልሱ ነበር።

22. “ይህም ድኻ ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም ዕቅፍ ወሰዱት። ሀብታሙም ሰው ደግሞ ሞቶ ተቀበረ።

23. በሲኦልም እየተሠቃየ ሳለ ቀና ብሎ ከሩቅ አብርሃምን አየ፤ አልዓዛርንም በዕቅፉ ይዞት አየ።

24. እርሱም፣ ‘አብርሃም አባት ሆይ፤ ራራልኝ፤ በዚህ ነበልባል እየተሠቃየሁ ስለ ሆነ፣ አልዓዛር የጣቱን ጫፍ ውሃ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ እባክህ ላክልኝ’ እያለ ጮኸ።

25. “አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ በምድራዊ ሕይወትህ ዘመን መልካም ነገሮችን እንደ ተቀበልህ፣ አልዓዛርም ደግሞ ክፉ ነገሮችን እንደ ተቀበለ አስታውስ፤ አሁን ግን እርሱ እዚህ ሲጽናና፣ አንተ በሥቃይ ላይ ትገኛለህ።

26. ከሁሉም በላይ ከዚህ ወደ እናንተ ለማለፍ የሚፈልጉ እንደማይችሉ፣ እዚያ ያሉትም ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ፣ በእኛና በእናንተ መካከል ትልቅ ገደል ተደርጎአል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 16