ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 7:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ።እርሱም ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ፣ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን ልኮ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ የሚገባኝ ሰው አይደለሁምና አትድከም፤

7. ከዚህም የተነሣ በአንተ ፊት ለመቅረብ እንኳ እንደሚገባኝ ራሴን አልቈጠርሁም፤ ብቻ አንድ ቃል ተናገር፤ አገልጋዬ ይፈወሳል።

8. እኔ ራሴ የበላይ አለቃ አለኝ፤ ከበታቼም የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን፣ ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው የታዘዘውን ያደርጋል።”

9. ኢየሱስም ይህን ሲሰማ በእርሱ ተደነቀ፤ ዘወር ብሎም ይከተለው ለነበረው ሕዝብ፣ “እላችኋለሁ፤ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት በእስራኤል እንኳ አላገኘሁም” አላቸው።

10. የተላኩት ሰዎችም ወደ ቤት በተመለሱ ጊዜ፣ አገልጋዩን ድኖ አገኙት።

11. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብዙ ሳይቈይ፣ ናይን ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱና ብዙ ሕዝብም አብረውት ሄዱ።

12. ወደ ከተማዋ መግቢያ በር ሲደርስም፣ እነሆ፤ ሰዎች የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው ከከተማዋ ወጡ፤ ሟቹም ለእናቱ አንድ ልጅ ብቻ ነበር፤ እናቱም መበለት ነበረች፤ ብዙ የከተማውም ሕዝብ ከእርሷ ጋር ነበረ።

13. ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፣ “አይዞሽ፤ አታልቅሺ” አላት።

14. ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ሰዎች ቀጥ ብለው ቆሙ፤ ኢየሱስም፣ “አንተ ጐበዝ፤ ተነሥ እልሃለሁ” አለው።

15. የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ። ኢየሱስም ወስዶ ለእናቱ ሰጣት።

16. ሁሉም በፍርሀት ተውጠው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ “ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነሥቶአል፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ጐብኝቶአል” አሉ።

17. ይህም የኢየሱስ ዝና በመላው ይሁዳና በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ወጣ።

18. የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህንን ሁሉ ለዮሐንስ ነገሩት። እርሱም ከመካከላቸው ሁለቱን ጠርቶ፣

19. “ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? በሉት” ብሎ ወደ ጌታ ላካቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 7