ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 18:15-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ በመሆኑ፣ እናንተው ጨርሱት፤ እኔ በእንዲህ ዐይነት ነገር ፈራጅ ለመሆን አልሻም።”

16. ስለዚህ ከፍርድ ወንበር ፊት አስወጣቸው።

17. በዚህ ጊዜ ሁሉም የምኵራቡን አለቃ፣ ሶስቴንስን ይዘው በፍርድ ቤቱ ፊት ደበደቡት፤ ጋልዮስ ግን ነገሩ ደንታም አልሰጠውም።

18. ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ብዙ ቀን በቆሮንቶስ ተቀመጠ፤ ከዚያም ወንድሞችን ተሰናብቶ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋር በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ። ስእለትም ስለ ነበረበት ክንክራኦስ በተባለ ቦታ ራሱን ተላጨ።

19. ኤፌሶን በደረሰ ጊዜም ጵርስቅላንና አቂላን እዚያው ተዋቸው፤ እርሱ ራሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር።

20. ከእነርሱ ጋር እንዲሰነብት በጠየቁትም ጊዜ ፈቃደኛ አልሆነም፤

21. ነገር ግን ሲለያቸው፣ “የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ ተመልሼ እመጣለሁ” አላቸው፤ ከኤፌሶንም ተነሥቶ በመርከብ ተጓዘ።

22. ቂሳርያም በደረሰ ጊዜ፣ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቀረበ፤ ከዚያም ወደ አንጾኪያ ወረደ።

23. በአንጾኪያም ጥቂት ጊዜ ከቈየ በኋላ፣ ከዚያ ተነሥቶ በገላትያና በፍርግያ አገሮች ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ደቀ መዛሙርትን ሁሉ አበረታታ።

24. በዚህ ጊዜ የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነ አጵሎስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ እርሱም የተማረና ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር።

25. ይህ ሰው፣ የጌታን መንገድ የተማረ፣ ስለ ኢየሱስም በትክክል የሚናገርና በመንፈስ እየተቃጠለ የሚያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ እርሱ የሚያውቀው የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር።

26. እርሱም በምኵራብ በድፍረት ይናገር ጀመር፤ ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፣ ወደ ቤታቸው ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ይበልጥ አስተካክለው አስረዱት።

27. አጵሎስ ወደ አካይያ ለመሄድ በፈለገ ጊዜ፣ ወንድሞች አበረታቱት፤ በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርትም እንዲቀበሉት ደብዳቤ ጻፉለት። እዚያም በደረሰ ጊዜ ከጸጋው የተነሣ አምነው ለነበሩት ትልቅ ረዳት ሆናቸው፤

28. ከቅዱሳት መጻሕፍት እያመሳከረ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከአይሁድ ጋር በጽኑ በመከራከር በሕዝብ ፊት ይረታቸው ነበርና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 18