ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 5:20-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. “ሂዱ፤ በቤተ መቅደሱም አደባባይ ቁሙ፤ የዚህንም ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ ንገሩ” አላቸው።

21. እንደ ነጋም፣ በተነገራቸው መሠረት፣ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገብተው ሕዝቡን ማስተማር ጀመሩ።ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው የአይሁድን ሸንጎና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጉባኤ በሙሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ላኩ።

22. የተላኩትም ወደ እስር ቤቱ ሄደው በዚያ አላገኟቸውም፤ ተመልሰውም እንዲህ አሏቸው፤

23. “እስር ቤቱ በሚገባ ተልፎ፣ ጠባቂዎቹም በበሩ ላይ ቆመው አገኘን፤ ከፍተን ስንገባ ግን በውስጡ ማንም አልነበረም።”

24. የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ሹምና የካህናት አለቆችም ይህን በሰሙ ጊዜ በነገሩ ተገረሙ፤ ግራም ተጋቡ።

25. በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ፣ “እነሆ፤ እስር ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆመው ሕዝቡን እያስ ተማሩ ናቸው” አላቸው።

26. የጥበቃ ሹሙም ከወታደሮቹ ጋር ሄዶ፣ ይዞ አመጣቸው፤ ያመጧቸው ግን ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግሯቸው ስለ ፈሩ በኀይል ሳያስገድዱ ነበር።

27. ሐዋርያትንም አምጥተው በሸንጎው ፊት አቆሟቸው፤ ሊቀ ካህናቱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤

28. “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ ደግሞም እኛን ለዚህ ሰው ደም ተጠያቂዎች ልታደርጉን ቈርጣችሁ ተነሣችሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 5