ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 11:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም ሸምበቆ የመሰለ መለኪያ በትር ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ፤ “ሄደህ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን ለካ፤ በዚያም የሚያመልኩትን ቊጠር።

2. የውጭውን አደባባይ ግን ተወው፤ አትለካው፤ ለአሕዛብ የተሰጠ ነውና። እነርሱ የተቀደሰችውን ከተማ አርባ ሁለት ወር ይረግጧታል።

3. ለሁለቱ ምስክሮቼ ኀይል እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ትንቢት ይናገራሉ።”

4. እነዚህም በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙት ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።

5. ማንም እነርሱን ሊጐዳ ቢፈልግ፣ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ያጠፋል፤ ሊጐዳቸው የሚፈልግ ሁሉ መሞት ያለበት በዚህ ዐይነት ነው።

6. እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ ደግሞም ውሃዎችን ወደ ደም ለመለወጥ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ምድርን በማንኛውም መቅሠፍት ለመምታት ሥልጣን አላቸው።

7. ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ድል ይነሣቸዋል፤ ይገድላቸዋልም።

8. ሬሳቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጣላል፤ ይህች ከተማ ሰዶምና ግብፅ እየተባለች በምሳሌ የምትጠራውና የእነርሱም ጌታ የተሰቀለባት ናት።

9. ከወገን፣ ከነገድ፣ ከቋንቋና ከሕዝብ የመጡ ሰዎች ሬሳቸውን ሦስት ቀን ተኩል ይመለከታሉ፤ ሬሳቸውም እንዳይቀበር ይከለክላሉ።

10. እነዚህ ሁለት ነቢያት የምድር ነዋሪዎችን ያሠቃዩ ስለ ነበር፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በእነርሱ ላይ በደረሰው ደስ ይላቸዋል፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይለዋወጣሉ።

11. ከሦስቱ ቀን ተኩል በኋላ ግን፣ የሕይወት እስትንፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶ ገባባቸው፤ እነርሱም ተነሥተው በእግሮቻቸው ቆሙ፤ ይመለከቷቸውም በነበሩት ላይ ታላቅ ድንጋጤ ወረደባቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 11