ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 11:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ ደግሞም ውሃዎችን ወደ ደም ለመለወጥ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ምድርን በማንኛውም መቅሠፍት ለመምታት ሥልጣን አላቸው።

7. ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ድል ይነሣቸዋል፤ ይገድላቸዋልም።

8. ሬሳቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጣላል፤ ይህች ከተማ ሰዶምና ግብፅ እየተባለች በምሳሌ የምትጠራውና የእነርሱም ጌታ የተሰቀለባት ናት።

9. ከወገን፣ ከነገድ፣ ከቋንቋና ከሕዝብ የመጡ ሰዎች ሬሳቸውን ሦስት ቀን ተኩል ይመለከታሉ፤ ሬሳቸውም እንዳይቀበር ይከለክላሉ።

10. እነዚህ ሁለት ነቢያት የምድር ነዋሪዎችን ያሠቃዩ ስለ ነበር፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በእነርሱ ላይ በደረሰው ደስ ይላቸዋል፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይለዋወጣሉ።

11. ከሦስቱ ቀን ተኩል በኋላ ግን፣ የሕይወት እስትንፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶ ገባባቸው፤ እነርሱም ተነሥተው በእግሮቻቸው ቆሙ፤ ይመለከቷቸውም በነበሩት ላይ ታላቅ ድንጋጤ ወረደባቸው።

12. ከዚያም፣ “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸው እየተመለከቷቸው በደመና ወደ ሰማይ ወጡ።

13. በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማዪቱም አንድ ዐሥረኛ ወደመ፤ በነውጡም ሰባት ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ የተረፉትንም ፍርሀት ያዛቸው፤ ለሰማይም አምላክ ክብር ሰጡ።

14. ሁለተኛው ወዮ ዐልፎአል፤ እነሆ፤ ሦስተኛው ወዮ ቶሎ ይመጣል።

15. ሰባተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፤“የዓለም መንግሥት፣የጌታችንና የእርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”

16. በእግዚአብሔር ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ የተቀመጡት ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤

17. እንዲህም አሉ፤“ያለህና የነበርህ፣ሁሉን ቻይ፤ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እናመሰግንሃለን፤ምክንያቱም አንተ ታላቁን ኀይልህን ይዘህ ነግሠሃል።

18. አሕዛብ ተቈጥተው ነበር፤የአንተም ቍጣ መጣች፤በሙታን ላይ የምትፈርድበት፣ለአገልጋዮችህ ለነብያት፣ለቅዱሳንና ስምህን ለሚፈሩት፣ለታናናሾችና ለታላላቆች ዋጋቸውን የምትሰጥበት፣ምድርንም ያጠፏትን የምታጠፋበት ዘመን መጣ።”

19. ከዚያም በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተ፤ በመቅደሱም ውስጥ የኪዳኑ ታቦት ታየ፤ መብረቅ፣ ድምፅ፣ ነጐድጓድ፣ የምድር መናወጥና ታላቅም በረዶ ሆነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 11