ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤፌሶን 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለአሕዛብ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ

1. በዚህም ምክንያት እኔ ጳውሎስ ለእናንተ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ሆኛለሁ።

2. ለእናንተ ጥቅም ሲባል ስለ ተሰጠኝ የእግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በርግጥ ሰምታችኋል፤

3. ቀደም ሲል በአጭሩ እንደ ጻፍሁት፣ በመገለጥ እንዳውቀው የተደረገው ምስጢር ይህ ነው።

4. እንግዲህ ይህን ስታነቡ፣ የክርስቶስን ምስጢር እንዴት እንደ ማስተውል ለመረዳት ትችላላችሁ።

5. ይህም ምስጢር አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋርያትና ነቢያት የተገለጠውን ያህል ባለፉት ዘመናት ለነበሩ ሰዎች አልተገለጠም ነበር።

6. ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካይነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው።

7. እኔም በኀይሉ አሠራር በተሰጠኝ በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኛለሁ።

8. ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ።

9. እንዲሁም ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ላለፉት ዘመናት የተሰወረውን የዚህን ምስጢር አሠራር ለሁሉም እገልጥ ዘንድ ተሰጠኝ።

10. አሳቡም በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት አለቆችና ባለ ሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው፤

11. ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን በፈጸመው ዘላለማዊ ዕቅዱ መሠረት ነው።

12. በእርሱና በእርሱ ላይ ባለን እምነት አማካይነት፣ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን።

13. ስለዚህ ክብራችሁ በሆነው ስለ እናንተ በደረሰብኝ መከራ ተስፋ እንዳትቈርጡ ዐደራ እላችኋለሁ።

ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የተደረገ ጸሎት

14. በዚህም ምክንያት በአብ ፊት እንበረከ ካለሁ፤

15. ከእርሱም በሰማይና በምድር ያለ ቤተ ሰብ ሁሉ ስያሜ ያገኛል።

16. በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤

17. ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣

18. የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው።

19. እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።

20. እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣

21. በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን፤ አሜን።